ቀጥታ፡

''ጥርን በባህር ዳር'' የቱሪዝም እንቅስቃሴን የበለጠ በሚያነቃቃ መልኩ ይከበራል

ባህር ዳር፤ ታህሳስ 23/2018(ኢዜአ)፦“ጥርን በባሕርዳር”   የቱሪዝም እንቅስቃሴን የበለጠ በሚያነቃቃ መልኩ እንደሚከበር የባህር ዳር ከተማ የአስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገለፁ። 

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ''ጥርን በባህር ዳር'' የተለያዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

‎በኹነቱ ለመታደም የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዐቢይና ንዑሳን ኮሚቴዎችን ቀደም ብሎ በማቋቋም ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።


 

በአሉ  የቱሪዝም እንቅስቃሴን የበለጠ በሚያነቃቃ መልኩ  በተለያዩ ኹነቶች እንደሚከበር ጠቁመው ለዚህም በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ሆቴሎች፣ ሎጆችና ሪዞርቶችም እንግዶችን በተሻለ የእንግዳ አቀባበል ባህልና ወግ ለመቀበል ዝግጅት በማጠናቀቅ እንግዶችን እየተጠባበቁ እንደሚገኙም አንስተዋል።

‎ከተማዋ ለኑሮና ለጎብኝዎች የምትመች ውብና ማራኪ እንድትሆን ለማድረግ የሚያስችሉ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ከጣና ሀይቅ ዳርቻዎች ጋር ተሳስሮ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማትም የቱሪስትን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ታሳቢ ተደርጎ ተሰርቷል ብለዋል።


 

በቀጣይ ቀናትም የኪነ ጥበብ የባህል ፌስቲቫል፣ የገና ጨዋታ፣ የመፅሐፍ አውደ ርዕይና የማዕድ የማጋራት መርሃ ግብሮች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

እንዲሁም የከተራና የጥምቀት በዓላት አከባበርን ጨምሮ የብስክሌት ሽርሽር ፣ የታንኳ ቀዘፋና ሌሎች የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ መርሃ ግብሮችም እንደሚከናወኑ አመላክተዋል።


 

ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት ዝግጅት መኖሩንም ጠቅሰው፤ ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም የዝግጅቶቹ ማብቂያ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

የባህር ዳር ከተማ የሰላምና የልማት ከተማ መሆኗን ጠቁመው ዜጎች ወደ ከተማዋ በመምጣት ጥርን በባህር ዳር  እንዲታደሙና የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም