ቀጥታ፡

የባሕር ዳር ጄኔራል ፍሌክሴብልና ፋውንደሪ ፋብሪካ ተኪ ምርቶችን በማቅረብ ውጤታማ ሆኗል

ባሕርዳር፤ ታህሳስ 23/ 2018(ኢዜአ)፡- የባሕር ዳር ጄኔራል  ፍሌክሴብልና ፋውንደሪ  ፋብሪካ  በጥራትና በበቂ ሁኔታ ተኪ ምርቶችን በማቅረብ ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ። 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር  መላኩ አለበል እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የባሕር ዳር ጄኔራል  ፍሌክሴብልና ፋውንደሪ ፋብሪካን  ጎብኝተዋል።

ፋብሪካው ለስኳርና ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች የተደራጀ መለዋወጫዎችን በጥራትና በበቂ ሁኔታ ተኪ ምርቶችን ማቅረብ እንደሚችል ተመልክቷል። 

በጉብኝቱ ወቅት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር  መላኩ አለበል እንደገለጹት፤ የብሔራዊ የኢንዱስትሪ ምክር ቤት በቅርቡ በአማራ ክልል የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።


 

በዚህም የገበያ ትስስር ክፍተት እንዳለ መታየቱን ጠቅሰው፤ ይህም ፋብሪካዎቹ ከውጭ የሚያስገቧቸውን መለዋወጫዎች በመተው የሀገር ውሰጥን እንዲጠቀሙ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን  አውስተዋል።

የባሕር ዳር ጄኔራል  ፍሌክሴብልና ፋውንደሪ  ፋብሪካ የተደራጀና መለዋወጫዎችን በጥራትና በበቂ ሁኔታ ማቅረብ እንደሚችል ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።

ይህ  የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፉ የኢትዮጵያን እድገት በተሰላጠ ሁኔታ ይበልጥ ከፍ ለማድረግ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

ይህን ታሳቢ በማደረግ ከፖሊሲ፣ ስትራቴጂና  የሰው ሃይል አደረጃጀቶችን ማሻሻል በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት  እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ  ዋዩ ሮባ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለስኳር ፋብሪካ መለዋወጫ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ውስን በመሆናቸው ግብዓቶችን ከውጭ በማስመጣት ይጠቀማሉ።


 

የጎበኙት ፋብሪካ  ከውጭ የሚመጡ መለዋወጫዎችን ማምረት የቻለና ተወዳዳሪ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ለስኳር ፋብሪካዎች ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ምክትል ስራ አስኪያጅ አብነት አጥናፉ፤  የብረታ ብረት ፋብሪካው የመለዋወጭ ችግርን በሀገር ውስጥ መፍታት እንደቻለ መረዳታቸውን ተናግረዋል። 


 

እስካሁን መለዋወጫዎችን ከውጪ ሲያስመጡ እንደነበር አስታውሰው፤  በቀጣይ ከዚሁ የብረታ ብረት ፋብሪካ እንደሚጠቀሙ አስታውቀዋል።

ፋብሪካው የውጭ ምንዛሪ ማስገኘትና ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች መለዋወጫዎችን ማምረት ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ነው ያሉት የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዘላለም በላይ ናቸው።


 

የዛሬው ጉብኝት የገበያ ትስስር በማስፋት የገቢ አቅምን ለማሳደግ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በጉብኝቱ ላይ የፌዴራልና የክልል የዘርፉ አመራሮች እንዲሁም  የተለያዩ ፋብሪካዎች  አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም