ቀጥታ፡

ጠንካራ የቴክኖሎጂ ዐቅምን ለመፍጠር የምርምር ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል-ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አባበ፤ታኅሣስ 23/2018 (ኢዜአ)፡-ጠንካራ የቴክኖሎጂ ዐቅምን ለመፍጠር ዘመን ተሻጋሪ የምርምር ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስገነዘቡ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የምርምርና ልማት ፖሊሲ ምረቃና የማዕከል ምሥረታ ተካሂዷል።


 

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዚሁ ወቅት፤ ጥናትና ምርምር የአንድን ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ወታደራዊ ዐቅምን በመገንባት የማድረግና የመፈፀም ችሎታን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።

ከተቋም አልፎ ለሀገራችን ብሎም ለአኅጉራችን ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ የምርምር ሥራዎችን በመሥራትና በማዳበር አዳዲስ ግኝቶችን ልናበለፅግ ይገባል ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል።

ታላቅ ሀገርና ተቋም መገንባት የሚቻለው ሁል ጊዜ አዳዲስ ሐሳቦችን በማፍለቅ፣በማዳበር፣ በመከታተልና በመመራመር ነው ሲሉም አብራርተዋል።

በዚህም መሠረት ችግር ፈቺ እና የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም በዘላቂነት የሚያስጠብቁ ጠንካራ የቴክኖሎጂ ዐቅሞችን በመፍጠር ዘመን ተሻጋሪ የልማትና የምርምር ሥራዎችን በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።


 

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ለሠራዊቱ የትራንስፎርሜሽን ጉዞ ስኬት የማይተካ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል ብለዋል።

በተጨማሪም ለዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ እንደ ማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ያገለግላል ማለታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኢዜአ የላከው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በደኅንነትና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ቀዳሚ የሐሳቦችና የፈጠራዎች ማዕከል በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ተቋም እንዲሆን አስቻይ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም