ኢትዮጵያ የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎቷን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችላትን አቅም እየገነባች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎቷን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችላትን አቅም እየገነባች ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎቷን በራስ አቅም ለመሸፈንና ከተረጂነት ለመላቀቅ የሚያስችላትን አቅም እየገነባች መሆኑ ተመላከተ።
በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት በርካታ ስትራቴጂካዊ የግብርና ኢኒሼቲቮች እየተተገበሩ ይገኛል።
በዚህም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ ኩታ ገጠም እርሻ ልማት፣ የሩዝ ምርት፣ የቅባት እህሎችና የጥራጥሬ ምርታማነትን የማሻሻል የልማት ሥራዎች ውጤት እያስገኙ ነው።
እነዚሁ ተነሳሽነቶችም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በመሸጋገርና የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ ወሳኝ የልማት እርምጃዎች ናቸው።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የግብርና ልማት ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ሚኒስቴሩ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋፋት እንዲሁም የጥሬ ዕቃዎችን አቅርቦት ለማሳደግ ግብ ይዞ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በግብርናው መስክ የተመዘገቡ ውጤቶች ዘርፉ እመርታዊ ለውጥ እያመጣ ለመሆኑ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዓመቱን ሙሉ ማምረት እንዲችሉ ዕድል መፈጠሩንም ጠቁመዋል።
የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ዓለማየሁ ወጫቶ (ዶ/ር)፤ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተሰሩ ሥራዎች በመጠባበቂያ ክምችት ከፍተኛ አቅም እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
በሁሉም የግብርና ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችም የሰብዓዊ ድጋፍ መጠባበቂያ ክምችት አቅም መጎልበት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም በፌዴራልና በክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት የሚውል መጠባበቂያ እህል ክምችት ምርት ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቡን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ክልሎች በሶስት ዙር ለሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ አሰጣጥ የሚውሉ ምርቶችን ለመጠባበቂያ ክምችት ገቢ እያደረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህም የኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል የእህል መጠባበቂያ ክምችት አቅም በትክክለኛው መንገድ ላይ እየተመራ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።