ባንኩ በሚዛን አማን ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካማ ወገኖች ለገና በዓል መዋያ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ በሚዛን አማን ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካማ ወገኖች ለገና በዓል መዋያ ድጋፍ አደረገ
ሚዛን አማን፤ ታኅሣሥ 23/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምዕራብ ሪጅን ጅማ ዲስትሪክት መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ በሚዛን አማን ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካማ ወገኖች ለበዓል መዋያ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረገ።
የዲስትሪክቱ ዳይሬክተር አቶ ሳድቅ አብዶ እንደገለጹት ባንኩ ዛሬ የበዓል መዋያ ድጋፍ ያደረገው በሚዛን አማን ከተማ ለሚገኙ 200 አቅመ ደካሞች ነው።
በዚህም ለእያንዳንዳቸው የዘይት፣ የዳቦ ዱቄትና የዶሮ መግዣ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ገልጸው፣ ለተደረገው ድጋፍም ባንኩ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል ብለዋል።
ባንኩ ድጋፉን ያደረገው ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም በተለያዩ በዓላት ለአቅመ ደካማ ወገኖች የሚያደርገውን የማዕድ ማጋራት ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በድጋፍ መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ታገል ወንድሙ በበኩላቸው ማዕድ ማጋራት ባህል እየሆነ በመምጣቱ አቅም የሌላቸው በርካታ ወገኖች እየተደገፉ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት ለሰው ተኮር የልማት ሥራዎች ትኩረት መስጠቱን ገልጸው፣ የማህበረሰቡ እርስ በርስ የመተጋገዝና በዓላትን በመረዳዳት የማሳለፍ እሴት ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት መሰል ድጋፎች እንዲደረጉም ከተማ አስተዳደሩ የማስተባበር ሥራዎችን እንደሚያከናውን ተናግረዋል።
ዛሬ ድጋፍ ከተደረገላቸው ወገኖች መካከል አቶ ሚሊዮን ገብሬ በዓሉን ያለሀሳብ ማሳለፍ እንዲችሉ ድጋፍ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ምንም ጧሪና ተንከባካቢ እንደሌላቸውና በእርጅና ምክንያት በችግር ውስጥ እንደሚኖሩ ገልጸው፣ ባንኩ ይህንን በማየት ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።
በማዕድ ማጋራት መርሃግብር ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮ ካሰች ኑርዬ የተደረገላቸው ድጋፍ መጪውን የገና በዓል ከልጃቸው ጋር ያለሀሳብ ለማሳለፍ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።