የኢትዮጵያ የዲጂታል ልማት ስትራቴጂ የመፍጠርና መተግበር አቅም የታየበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዲጂታል ልማት ስትራቴጂ የመፍጠርና መተግበር አቅም የታየበት ነው
መቀሌ ፤ታህሳስ 23/2018 (ኢዜአ) ፡-የኢትዮጵያ የዲጂታል ልማት ስትራቴጂ የመፍጠርና መተግበር አቅም የታየበት መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ።
የ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ ትግበራን ታኅሣሥ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።
ለእቅዱ ትግበራም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬት በመሰነቅ በቀጣይ በዘርፉ የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት የማስቀጠል ግብ የተቀመጠለት ነው።
በዚህም መሰረት ተደራሽነትን፣ ለዜጎች እኩል እድል መፍጠርንና በዜጎችና በተቋማት መካከል መተማመንን የማጎልበት ዓላማ በማንገብ ለስኬቱ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ በትግራይ ክልል መቀሌ ያነጋገራቸው በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አይ ሲቲ ኤጀንሲ የዘርፉ ባለሙያዎች የዲጂታል አገልግሎት ከፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎትም ባለፈ ለብልሹ አሰራር ምክንያቶች ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ከባለሙያዎቹ መካከል የአይ ሲቲ ባለሙያ የሆኑት አቶ እያሱ ተካ፤ የዲጂታል ልማትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ዘመኑ የሚጠይቀው የሀገራት መወዳደሪያ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ያለፉት ዓመታት ትግበራና ቀጣይ የተያዘው እቅድ በዘርፉ የሌሎች አገራት ተከታይ ከመሆን ይልቅ የመፍጠርና መተግበር አቅም የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
የዲጂታል አገልግሎት አሰራር ፈጣን አገልግሎት ከመስጠቱም ባለፈ የብልሹ አሰራር ምክንያት የሚሆኑ ክፍተቶችን የሚዘጋ ነው ብለዋል።
የሃርድዌርና ሶፍት ዌር ጥገና ከፍተኛ ባለሙያው ዮውሃንስ ለአከ በበኩሉ የደረስንበት ዘመን የመፍጠርና የመፍጠን በመሆኑ በዲጂታል ዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን በዚሁ ልክ መጓዝ ይኖርብናል ሲል ተናግሯል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ልማት እያደረገች ያለችው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስቶ ለቀጣይ እቅዶች የላቀ ስኬት የሁላችንም ጥረትና እገዛ ያስፈልጋል ብሏል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ የተከናወነው ተግባር ከፍተኛ የሚባል ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን የገለፀው ደግሞ ሌላኛው የሶፍትዌር እና ሃርድዌር ጥገና ባለሙያ ወጣት አረጋይ ገብረመስቀል ነው።
በዲጂታል ልማት የብዙ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ከወረቀት ነፃ እንዲሆን መደረጉን አንስቶ የባንኮችና የቴሌኮም አገልግሎትም መሰረታዊ ለውጥ የመጣበት ስለመሆኑ አንስቷል።
በመሆኑም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እቅድ በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን የመንግስት ጥረት እንዳለ ሆኖ የባለሙያዎችና የሚመለከታቸው አካላት ጥረት ሊታከልበት ይገባል ብሏል።