የኢትዮጵያ የቡና ምርታማነት የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አቅም እየፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የቡና ምርታማነት የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አቅም እየፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የቡና ምርታማነት ዓለም አቀፍ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አቅም እየፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።
ኢትዮጵያ የግብርናውን ምርታማነት የሚያሳድጉ የተሻሻሉ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች።
የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ዋነኛ ምንጭ የሆነው ቡናም የዚህ አካል ሲሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታት በቡና ምርታማነት ላይ በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል።
መንግስት ቡናን በብዛት፣ በጥራትና ዓለም አቀፍ ፍላጎትን ባገናዘበ መልኩ በማምረት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ያለው አበርክቶ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ያረጁ የቡና ተክሎችን በአዲስ የመተካት እንዲሁም ቴክኖሎጂን የመጠቀም ባህል እያደገ መምጣቱ በቡና ምርታማነትና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ከፍተኛ ለውጥ አንዲመዘገብ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በተለይም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ የቡና ችግኞች የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ አቅም እየፈጠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የቡና ምርታማነትን ለማሻሻል የተደረጉ የሪፎርም ሥራዎች ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ በከፍተኛ መጠን ማሳደግ ማስቻላቸውን ገልጸዋል።
የለውጡ መንግስት በ2013 ዓ.ም የሪፎርም ሥራውን ሲጀመር ከቡና ወጪ ንግድ 907 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውሰው በ2014 ዓ.ም ደግሞ ገቢው ወደ አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር ማደጉን ጠቅሰዋል።
የሪፎርሙ ስኬታማ ጉዞ ለዘርፉ በፈጠረው መልካም ዕድል በመታገዝ በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት አምስት ወራት ከቡና ወጪ ንግድ አንድ ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል።
ጥሬ ቡናን ብቻ ከመላክ ባለፈ ዕሴት የተጨመረበት የቡና ምርትን ለዓለም ገበያ ለማስተዋወቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማኅበር ፕሬዝዳንት ሁሴን አምቦ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ በማሳደግና የተሻሻሉ የቡና ችግኞች እንዲሰራጩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት 600 ሺህ ቶን የቡና ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከሶስት ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።