የቱሪስት ፍላጎትን ያማከለ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የሰው ኃይል ልማት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪስት ፍላጎትን ያማከለ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የሰው ኃይል ልማት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2018(ኢዜአ)፦ የቱሪስት ፍላጎትን ያማከለ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የሰው ኃይል ልማት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በብዝሃ ዘርፍ የዕድገት ምንጭነት ከተለዩ መስኮች መካከል ቱሪዝም አንዱ ነው።
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፉ ያልተነካ እምቅ አቅም ቢኖራትም ሃብቶቿን በአግባቡ በመለየትና በማልማት ረገድ ውስንነቶች ነበሩ፡፡
የለውጡ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ነባር የመስህብ ስፍራዎችንና መዳረሻዎችን ከማደስ ባሻገር አዳዲስና ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪስት ቦታዎችን በማልማት ከፍተኛ መነቃቃት እየፈጠረ ይገኛል፡፡
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይታሰብ ስዩም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ አመርቂ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለቱሪዝም ዘርፍ እድገት ወሳኝ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው ይህንኑ እምቅ ሃብት በአግባቡ እና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመጠቀም የሰለጠነ የሰው ኃይል ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ የቱሪስት ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የሰው ኃይል ልማት ላይ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ተማሪዎች የተለያዩ ቋንቋዎችን እንዲማሩ በማድረግና የተግባቦት ክህሎታቸውን በማዳበር የሀገራቸውን ባህልና ትውፊት በሚገባ እንዲያስተዋውቁ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ ዘርፉን የበለጠ ለማሳደግ የሚረዱ የተለያዩ ስልጠናዎችን በኦንላይን ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሰልጣኝ ተማሪዎች በበኩላቸው ዘርፉን በሚገባ የተረዳና የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ ለመጠቀምና ለሌሎች ለማስተዋወቅ ይረዳል ብለዋል።
የቱሪዝም ማኔጅመንት ተማሪ የሆነችው ናርዶስ ወልዴ ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪዝም መስህብና አስደናቂ ተፈጥሮ ያላት ሀገር መሆኗን በማንሳት፥ በዘርፉ የሚሰጡ ትምህርትና ስልጠናዎች የመስህብ ህብትን በእውቀት ለማስተዋወቅ ትልቅ አቅም ይሆናሉ ብላለች።
የቱር ጋይድ ተማሪ ሐሰን ዘይኑ በበኩሉ መንግስት በርካታ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ማከናወኑን በማንሳት፥ በተማረው ሙያ ሀገሩን ለማስተዋወቅና ጎብኚዎችን ለመሳብ እንደሚሰራ ተናግሯል።
ኢትዮጵያ ያላትን ታሪክና የቱሪዝም ሃብት በአግባቡ በመረዳት ለቱሪስቶች የተመቸ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አጋዥ ስልጠና እየወሰደች መሆኗን የቱር ጋይድ ተማሪዋ ፋሲካ ትዛዙ ገልጻለች።