የምክክር ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ለሚገኙ ተግባራት ስኬት የሁሉም ዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው - አፈ-ጉባኤዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ለሚገኙ ተግባራት ስኬት የሁሉም ዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው - አፈ-ጉባኤዎች
ሚዛን አማን፣ ታኅሣሥ 23/2018 (ኢዜአ):- የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ለሚገኙ ተግባራት ስኬት የሁሉም ዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን የተለያዩ ክልሎች አፈ-ጉባኤዎች ተናገሩ።
አፈ-ጉባኤዎቹ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን እያከናወናቸው ባሉ ተግባራት ሂደት ውስጥ የሕዝብ ተሳትፎ እንዲጠናከር ሲያከናውኑ የቆዩትን ህዝብ የማስተባበር ሥራን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በዚህም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ለሚገኙ ተግባራት ስኬት የሁሉም ዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑንም አፈ-ጉባኤዎቹ አክለዋል።
ከአፈ-ጉባኤዎቹ መካከል የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም እንዳሉት ምክክር ሁሉንም ዓይነት ያለመግባባት ችግሮችን ይፈታል።
ለዚህም በሀገራችን ውስጥ ያሉ አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ ሰላምና አንድነትን ለማጽናት ኮሚሽኑ የሚሠራቸው ሥራዎችን መደገፍ ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።
ሕዝቡ የምክክር አስፈላጊነት ላይ በቂ ግንዛቤ ይዞና አምኖበት እንዲደግፍ ሲያደርጉ የነበረውን የማስተባበር ተሳትፎ በውይይት ወቅትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ መሰረት ማቴዎስ በበኩላቸው ሰላም ለዕድገትና ልማት አስፈላጊ በመሆኑ ተመካክረን ሰላማችንን ዘላቂ ማድረግ አለብን ሲሉ ገልጸዋል።
መንግስት የምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ እያከናወነ ያለው ተግባር ለሕዝብ አንድነትና የአብሮነት ዕሴት መጎልበት ትልቅ ትኩረት እንደሰጠ ማረጋገጫ መሆኑን አንስተዋል።
በመግባባት ላይ የተመሠረተ አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት ተሳታፊዎች በመደማመጥ ሊወያዩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በሀገራዊ የልማት ሥራዎች ስኬት ላይ የታየው የህዝብ ተሳትፎ የምክክር ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ለሚገኙ ተግባራት ስኬት ሚናው የጎላ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አስካል አልቦሮ ናቸው።
ውይይቱ ስኬታማ እንዲሆን ማኅበረሰቡ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ የማድረግ ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች አፈ-ጉባኤዎች የጋራ ፎረም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሰሞኑን መካሔዱ ይታወሳል።