በሶማሌ ክልል 200 ሺህ ሰዎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን አጠናቀዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል 200 ሺህ ሰዎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን አጠናቀዋል
ጅግጅጋ፣ ታህሳስ 23/2018 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል 200 ሺህ ሰዎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ማጠናቀቃቸውን የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ገለጸ።
የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ መሀሙድ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የ5 ሚሊዮን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና 322 ሺህ ሰዎችን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል።
በዚህም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የመንግስት ሰራተኞች እና ሌሎች ከቴክኖሎጂው ጋር ቅርበትና ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ስልጠናውን በመስጠት በክልሉ 200 ሺህ ዜጎች ስልጠናውን አጠናቀዋል ብለዋል።
የኢትዮ ኮደርስ ኢንሼቲቭ በዘርፉ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ ለማፍራት እንዲሁም የሥራ ዕድልን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀሪው የበጀት ዓመቱ ወራትም ከ122 ሺህ በላይ ሰዎችን ለማሠልጠን ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ስልጠናውን በክልሉ በሚገኙ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በበየነ መረብ መውሰድ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ተማሪ ኩሬሽ መሀሙድ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወስደው ካጠናቀቁት መካከል ስትሆን ስልጠናው የቴክኖሎጂ እውቀቷን እንደጨመረው አንስታለች።
ስልጠናውን በበይነመረብ መውሰድ እንደሚቻል ከተነገረኝ በኋላ ስልጠናውን በመውሰድ አጠናቅቄያለሁ ብላለች።
ሌላኛዋ ተማሪ ፋጡማ ሹክር በበኩሏ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናውን በመውሠድ የቴክኖሎጂ እውቀቷን ማዳበር የሚያስችላትን በዳታ አናላይሲስ በማጠናቀቅ ሰርተፊኬት ማግኘቷን ተናገራለች።
ተማሪ ነስሪን ሁሴን በበኩሏ ስልጠናውን በበይነመረብ በመውሰድ ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅም እንዳሳደገች ተናግራለች።