የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ የፖሊስ ሠራዊት በማፍራት የማይተካ ሚና እየተጫወተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ የፖሊስ ሠራዊት በማፍራት የማይተካ ሚና እየተጫወተ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ የፖሊስ ሠራዊት በማፍራት የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የሶሰተኛ ዲግሪ(PhD) ትምህርት ፕሮግራም የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት፤ የትምህርት መርሃ ግብሩ ከሀገረ መንግስት ግንባታ ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያለውና ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፖሊስነት ተመራጭ የሙያ መስክ እንዲሆን በማስቻል በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ የፖሊስ ሠራዊት እንዲፈጠር እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
በጥናትና ምርምር ሥራም ዘመኑን የዋጀ የፖሊስ ሠራዊትና ዘመናዊ የፖሊስ ተቋም ግንባታ ሂደት የማይተካ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ለተሻለ የፖሊስ ሠራዊትና ተቋም ግንባታ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ በዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት መርሃ ግብር በፖሊስ ታሪክ የመጀመሪያው መሆኑን ገልጸዋል።
የትምህርት መርሃ ግብሩ መጀመር ዕውቀትና ብቃት ያለው የላቀና ተወዳዳሪ የፖሊስ ሠራዊትና ተቋም ለመገንባት ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲው በ19 የመደበኛ ዲግሪ እንዲሁም በዘጠኝ የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሃ ግብሮች ውጤታማ የሠራዊት አመራርና አባላትን እያፈራ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ታምራት ሙሉጌታ(ዶ/ር)፤ በትምህርትና ስልጠና፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች የተሰጠውን ተልዕኮ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለጎረቤት ሀገራት የፖሊስ ሠራዊት አባላትና መኮንኖች ጭምር ስልጠና እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሀገር ውስጥና በውጭ ምሁራን ተገምግሞ በዩኒቨርሲቲው የሶሰተኛ ዲግሪ ትምህርት መርሃ ግብር ለፖሊስ ሠራዊትና ተቋም ግንባታ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።