በጉጂ ዞን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በጉጂ ዞን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተገኝቷል
አዶላ፤ ታህሳስ 23/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መገኘቱን የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ነጋሽ ቡላላ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በዞኑ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ዘላቂ ሠላም ማስፈን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በእካሁኑ ሂደት በተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ የሆኑ የሰላም ግንባታና የልማት ስራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ ባለፉት አራት ወራት የመግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 174 የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በማስረከብ ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ይህንኑ ተከትሎ ለህብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መሳለጥ አመቺ ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል።
በዞኑ ያለው ሰላም ለልማት ስራዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመው በበጀት አመቱ ባለፉት ወራቶች ከ392 በላይ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በዞኑ በግንባታ ላይ ካሉ መካከል የንጽህ መጠጥ ውሀ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድና የመስኖ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ።
የዞኑ ህዝብ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በግልና በአካባቢ ጥበቃ በከተማ ጽዳትና ውብት እንዲሁም በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ግንባታ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የጉጂ ሆኩ አባገዳ ገናል አጋ በበኩላቸው ከመንግስት ጋር በትብብር መሰራቱ በዞኑ ለተገኘው ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመው በቀጣይም ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።
መንግስት በአስተዋይነትና በአርቆ አሳቢነት ላደረገው ያልተቋረጠ የሰላም ጥሪ ምስጋና አቅርበዋል።
በአካባቢው የሠላም ጥሪ ከተቀበሉ መካከል ወጣት እሸቱ ታሪኩ በሰጠው አስተያየት የተሳሳተ መንገድ በመከተል የበደለውን ህዝብ ለመካስ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
የሰላም አማራጭን ከመቀበል ውጪ አማራጭ የለም ያለው ወጣቱ ሌሎችም ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ እንዲሰጡ መልእክት አስተላልፏል።