ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ዘላቂ ሠላምና አብሮነትን ይበልጥ ለማጠናከር ሁነኛ መፍትሄ ነው

አሶሳ፤ ታህሳስ 23/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ዘላቂ ሠላምና አብሮነትን ይበልጥ ለማጠናከር ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

በርካታ ሀገራት መልካም እሴቶችን በመገንባት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ደግሞ በምክክር በማረምና በማስተካከል ዛሬ ላይ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት ችለዋል።

ከዚህ ተሞክሮ በመነሳትም በኢትዮጵያ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋትና እሴቶችን በመገንባት የግጭትና አለመግባባት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ይገባል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ የቆዩ ቁርሾዎችና አለመግባባቶች በምክክር እንዲፈቱ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሀገር ሽማግሌ አብዱልማህሙድ ኢብራሂም፤ ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ዘላቂ ሠላምና አብሮነትን ይበልጥ ለማጠናከር ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ አንድነት ለማንበር በምክክር ችግሮችን መፍታት የግድ መሆኑን አንስተው በመድረኩ ሁሉም በመሳተፍ እድሉን ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

ኮሚሽኑ በተለያየ ጊዜ በሚያዘጋጃቸው መድረኮችና አጀንዳ ልየታ ላይ መሳተፋቸውን ገልፀው፥ ምክክሩ አለመግባባቶችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ ገለታ ጋጋ፤ የሀገራዊ ምክክር መድረክ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል።

ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሔ በመስጠት በሀገር ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም በመያዝ ለሰላምና አብሮነት በጋራ መስራት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም