ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የዲጂታል አድራሻ በሁሉም ከተሞች ማስፋት ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የዲጂታል አድራሻ በሁሉም ከተሞች ማስፋት ያስችላል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ብሔራዊ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት በሁሉም ከተሞች ማስፋት እንደሚያስችል የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ታህሳስ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።
በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክትም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ተደራሽነትን የማስፋት፣ ለዜጎች እኩል ዕድል የመፍጠር፣ የዜጎችና ተቋማትን መተማመን የማጎልበት ቁልፍ ትልሞች እንዳሉት አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሕዝብ መገልገያ ዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በማስፋት የዜጎችን የዕለት ከዕለት ኑሮ በሰው ተኮር ዲጂታል ሥርዓት ማሻሻል እንደሚያስፈለግ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ ለኢዜአ እንገለጹት፤ የከተሞችን የመሠረተ ልማት ግንባታ ለማሳለጥ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት መሠረት ነው።
የዲጂታል አድራሻ መሠረተ ልማት የከተማ ይዞታን በዲጂታል መለያ በሚገባ በማስቀመጥ በዘመናዊ ሥርዓት የሚተዳደሩ ከተሞችን ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መነሻነት ብሔራዊ የዲጂታል አድራሻ መሠረተ ልማትን የማስፋት ሥራ በወሳኝ የትኩረት መስክ መያዙን ጠቁመዋል።
የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት በበርካታ ከተሞች በተለያየ ደረጃ በትግበራ ላይ እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትልሞች የብሔራዊ የዲጂታል አድራሻን ማስፋት በግልጽነት ላይ የተመሠረተ የአገልግሎትና የአስተዳደር ሥርዓት ለመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
ስትራቴጂው በሀገር አቀፍ ደረጃ በከተሞች የተጀመረውን ብሔራዊ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት በሁሉም ከተሞች ለማስፋት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ አንስተዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የከተሞችን ሁለንተናዊ የልማት ትስስር በማሰናሰል ዘመናዊ የአገልግሎትና የአስተዳደር ሥርዓት መሰረት መጣሉንም አስታውሰዋል።
በቀጣይም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የኮሙኒኬሽን መገናኛ መሠረተ ልማቶችን በራስ አቅም በማልማት ፍትሐዊ የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት እንደሚሰራ አስረድተዋል።