ቀጥታ፡

አልጄሪያ የምድቧ መሪ ሆና አጠናቀቀች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ አምስት የመጨረሻ ጨዋታዎች ተካሄደዋል።

በሙላይ ኤል ሀሰን ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ አልጄሪያ ኢኳቶሪያል ጊኒን 3 ለ 1 አሸንፋለች። 

ዚነዲን ቤላይድ፣ ፋሬስ ቻይቢ እና ኢብራሂም ማዛ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ኢሚሊዮ ንሱዌ ሎፔዝ ለኢኳቶሪያ ጊኒ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። 

አስቀድሞ ጥሎ ማለፍ የገባችው አልጄሪያ በዘጠኝ ነጥብ የምድቡ መሪ ሆና አጠናቃለች። 

አልጄሪያ ከናይጄሪያ በመቀጠል የምድብ ጨዋታዎቿን ያሸነፈች ሁለተኛ ሀገር ሆናለች።

በአንጻሩ በምድቡ ሶስተኛ ሽንፈቷን ያስተናገደችው ኢኳቶሪያል ጊኒ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃን በመያዝ ከውድድሩ ተሰናብታለች።


 

በተያያዘም ማምሻውን በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው የምድቡ ጨዋታ ቡርኪናፋሶ ሱዳንን 2 ለ 0 አሸንፋለች።

ላሲና ትራኦሬ እና አርሴኔ ኩዋሲ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። 

ሱዳን በ24ኛው ደቂቃ ያገኘችውን ፍጹም ቅጣት ምት አል ጎዞሊ ኖህ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቷን ያረጋገጠችው ቡርኪናፋሶ በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ሱዳን በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ምርጥ ሶስተኛ ሆና ጥሎ ማለፉን ተቀላቅላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም