ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ መጪውን የስኬት ዘመን በማለም እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ ታሪክን በመዘከር መጪውን የስኬት ዘመን በማለም እየተከበረ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ የሚገኝ ሲሆን የተማሪዎች ጥያቄና መልስ እንዲሁም የፊልም ውድድር የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።


 

በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው በኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማትና የትምህርት መስፋፋት ገንቢ ሚና እየተወጣ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ነው።

በዚህም በዩኒቨርሲቲው ባለፉት 75 ዓመታት ጉዞ ውስጥ በፖለቲካ መሪነት፣ በንግድና ሌሎች ዘርፎች ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ መድረክ ድረስ ስኬታማ ሰዎችን ማፍራት እንደቻለ ገልጸዋል።

የተማሪዎች የጥያቄና መልስ እንዲሁም የፊልም ውድድር ሥነ-ስርዓት አሸናፊዎች ብቃትና ተሰጥኦቸውን በሚገባ ማሳየት የቻሉበት መድረክ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዩኒቨርሲቲውን የራስ ገዝነት አካዳሚያዊ አስተዳደርም በጥንቃቄ በመምራት በስኬታማ መንገድ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ ክብረ በዓልም ታሪክን በመዘከር መጪውን ስኬት በማለም እየተከበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት በሰው ሃብት ልማት፣ በቴክኖሎጂና ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ አምጪ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል።

ከውድድሩ አሸናፊዎች መካከል በዩኒቨርሲቲው የ3ኛ ዓመት ተማሪ የማነ ጸሃዬ፤ በቆይታው ብቃትና ተሰጥኦውን የበለጠ በማጎልበት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚሰራ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም