ቀጥታ፡

የብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ አውደ ርዕዩ ምርቶቻችንን በማስተዋወቅ የተሳካ የገበያ ትስስር የፈጠርንበት ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ የሁለተኛው ብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ (ግሪን ሞቢሊቲ) አውደ ርዕይና ፎረም 2025 ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ የተሳካ የገበያ ትስስር የፈጠሩበት መሆኑን ተሳታፊዎች ገለጹ።

በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለአምስት ተከታታይ ቀናት የተካሄደው ሁለተኛው ብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ (ግሪን ሞቢሊቲ) አውደ ርዕይና ፎረም 2025 ተጠናቋል።


 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን በአውደ ርዕዩ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፤ በፎረሙ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተካሄዱ መድረኮች በርካታ ባለድርሻ አካላትን ማገናኘት የቻሉና ውጤታማ የመረጃ ልውውጥ የተደረገባቸው ናቸው።

ኢትዮጵያዊያን በዘርፉ የላቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ባቀረቡበት መድረክ ላይ በሻጮችና ሸማቾች መካከል የጠበቀ የገበያ ትስስር መፍጠሩን ተናግረዋል።


 

በሀገር አቀፍ ደረጃ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤታማ የብክለት ቀናሽ የትራንስፖርት አገልግሎት ምኅዳርን የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

አውደ ርዕይው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከማስተዋወቅ ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ስላለው ፋይዳ የጋራ ግንዛቤ የተፈጠረበት መሆኑን ገልጸዋል።

የሁለተኛው ብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ (ግሪን ሞቢሊቲ) አውደ ርዕይና ፎረም 2025 ተሳታፊዎች እንዳሉት፤ መድረኩ ለቀጣይ የንግድ ሥራቸው አቅም የፈጠረ ነው።

የቀርጫንሼ ግሩፕ የማኑፋክቸሪንግና አውቶሞቲቭ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቡበከር ይማም፤ በአውደ ርዕዩ ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ ሰፊ የገበያ ትስስር መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡


 

በቀጣይ ብክለት ቀናሽ የትራንስፖርት ተሽከርካሪ ተደራሽነትን በማስፋት የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ትልም ለማሳካት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የበላይነህ ክንዴ ሜታል ኢንጅነሪንግ የጥገና ሱፐርቫይዘር ሲሳይ በፍቃዱ በበኩላቸው፤ አውደ ርዕዩ ምርቶችቸውን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ደንበኞቻቸው በማስተዋወቅ ልምድ ያገኙበት መሆኑን አንስተዋል።


 

ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በአረንጓዴ አሻራና ሌሎች መስኮች አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገው ጥረት የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመቀነስ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ነው የተገለጸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም