ኢጋድ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ማስፈን ላይ በልዩ ትኩረት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
ኢጋድ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ማስፈን ላይ በልዩ ትኩረት ይሰራል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) በአዲሱ ዓመት በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ማስፈንና አካታች እድገትን ማረጋገጥ ላይ አበክሮ እንደሚሰራ የተቋሙ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ገለጹ።
ዋና ጸሀፊው የፈረንጆቹን 2026 አዲስ ዓመትን በማስመልከት የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዋና ፀሐፊው ሁሌም አዲስ ዓመትን በአዲስ ተስፋ እና የጋራ ህልም መጀመር ቀጣናዊ ጉዳዮችን በትብብር እልባት ለመስጠት ጥንካሬን እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ያለፈው ዓመት ቀጣናውን ግጭቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችና የኢኮኖሚ ጫናዎች ቢፈትኑትም የዜጎች አይበገሬነትና የቀጣናዊ አጋርነት ኃይል ጎልቶ መታየቱን አመልክተዋል።
ኢጋድ በአዲሱ ዓመት ሰላምን ለማስፈን፣ አይበገሬነትን ለማጠናከር እንዲሁም የሴቶች እና ወጣቶች ድምጽ በማጉላት በቀጣናው መጻኢ ጊዜ ላይ ያላቸውን ድርሻ ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ቀጣናዊ ተቋሙ የበለጠ ደህንነቱ የተረጋገጠ፣ አካታች እና ዜጎች ተስፋ የሚያደርጉት ቀጣና ለመፍጠር ከአባል ሀገራትና የልማት አጋሮች ጋር በትብብር መስራቱን ይቀጥላል ነው ያሉት።
አዲሱ ዓመት በቀጣናው ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጥበት እንዲሆንም ተመኝተዋል።