በአማራ ክልል የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎትን ማቀላጠፍ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎትን ማቀላጠፍ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ደብረ ማርቆስ፤ ታህሳስ 22/2018 (ኢዜአ)፡ -በአማራ ክልል የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎትን ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ የዲጅታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማጎልበት ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በደብረማርቆስ ከተማ አካሄዷል።
የክልሉ ሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ኃላፊ ማዓዛ በዛብህ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎችን በጠራ መረጃ ለማስደገፍ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በ8 "ሪጅኦ ፖሊታንት" ከተሞች በ204 ጣቢያዎች የተጀመረውን ሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ዲጅታላይዝድ በማድረግ ባለፉት 5 ወራት ብቻ ከ450 ሺህ በላይ የሞት፣ ጋብቻ፣ ፍቺና ልደት ኩነትን መመዝገብ መቻሉን አስረድተዋል።
የአሰራሩ ዲጂታላይዝ መደረጉም ከዚህ ቀደም በዓመት ለቅጻቅጽ ግዥ ይወጣ የነበረን ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን ተችሏል ብለዋል።
በመጀመሪያው ዙር የተገኘውን ተሞክሮ በማስፋት የ2ኛውን ዙር የዲጅታል ምዝገባ ስርዓት አጠናክሮ ለማስቀጠል የዛሬው መድረክ መከናወኑንም ገልጸዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ዲጅታል ኢትዮጵያ ቦዞኑ በአገልግሎት አሰጣጥ የነበረውን የተንዛዛ አሰራር መቀነስ አስችሏል ብለዋል።
የዛሬው መድረክ ዓላማም የምዝገባ ሂደቱን በዲጅታል በማከናወን ግልጽና ታማኒነት ያለው መረጃን ተደራሽ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ አቅም የሚፈጥር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ፤ የከተማ አስተዳደሩ በገቢዎች፣ በሲቪልና በቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት፣ በካዳስተርና ሌሎች የስራ መስኮች የዲጅታል አገልግሎት እየተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።