የክልሉን እምቅ የግብርና አቅም አሟጦ ለመጠቀም በጥናትና ምርምር ለማስደገፍ ትኩረት ተድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን እምቅ የግብርና አቅም አሟጦ ለመጠቀም በጥናትና ምርምር ለማስደገፍ ትኩረት ተድርጓል
ዲላ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያለውን እምቅ የግብርና አቅም አሟጦ ለመጠቀም በጥናትና ምርምር ለማስደገፍ ትኩረት መደረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ልማት አቅም ልየታ ላይ ያተኮረ መርሃ ግብር በዲላ ከተማ የተካሄደ ሲሆን ከውይይት መድረኩ በኋላ በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ ቱማታ ጭራቻ ቀበሌ 60 ሄክታር የቡና ኩታ ገጠም እርሻ የመስክ ምልከታ ተደርጓል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በማጠቃለያው እንዳሉት የክልሉን እምቅ የግብርና አቅም አሟጦ ለመጠቀም በጥናትና ምርምር ማስደገፍ ወሳኝ ነው።
በተለይ በክልሉ ያለውን ሰፊ መሬትና የውኃ ሀብት ከቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀመጠውን ግብ ወደ ተግባር ለመለወጥ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
ክልሉ በግብርና ልማት ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ትርፍ አምራች እንዲሆን ጥናትና ምርምርን መሰረት ያደረገ ስራ እንደሚሰራ አመልክተው የዛሬው መድረክም ይህንኑ ለማጠናከር የተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦችን በመተግበር ከፍተኛ ምርት ለማምረት የዘርፉ ባለድርሻ አካላትና አመራሩ በቅንጅት መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለግብርና ልማት ምቹ የሆነ ተፈጥሮ የታደለ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ ናቸው።
የግብርና አቅሞችን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ የአርሶ እና አርብቶ አደሩን ህይወት በመለወጥ ሀገርን ማሳደግ እንደሚቻልም ጠቅሰዋል።
በተለይም የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በኩል በክልሉ የሚስተዋለውን ውስንነት በመቅረፍ የግብርና ሽግግርን ማፋጠን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በእውቀት ላይ በመመስረት የሚከናወን የግብርና ልማት ስራ የኢትዮጵያን የግብርና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት ዋሳኝ ሚና እንደሚጫወትም አክለዋል።