ቀጥታ፡

የሀረር ከተማ የኮሪደር ልማት ስራዎችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ ነው

ሀረር፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ በሀረር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በሀረር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ እንደተናገሩትም የሀረር ከተማን ድምቀትና ውበት ይበልጥ የሚያጎናጽፉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።




ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ እንዲሁም ለመጪው ትውልድ መሰረት የሚጥሉ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው የኮሪደር ልማት ስራው አንዱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ በጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ ዙሪያ የቅርሱን ይዘት በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ቅርስን ጠብቆ ከማቆየት ባለፈ ትውልዱ በታሪክ እንዲወሳ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው የተጀመሩ የልማት ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

የተከናወኑና በሂደት ላይ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገዶች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ፋውንቴኖች፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎች፣ የአረንጓዴ ስፍራና የመንገድ ዳር መብራትን ያካተቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።




በሚሰሩ ስራዎች ህዝቡ እያደረገ የሚገኘው ትብብርና ድጋፍ ስራውን ከማገዝ ባለፈ ለበለጠ ውጤት የሚያነሳሳ መሆኑንም አስረድተዋል።

በየአካባቢው እየተከናወኑ ለሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች መሰረተ ልማት እንዲሟላ ከማስቻል ባሻገር ህገ ወጥነትን ለመከላከል ጭምር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም