ቀጥታ፡

በሀገራዊ ወግና ባህል የተቃኘ፣ ከዓለም እኩል መራመድ የሚያስችል ትምህርትና ሥልጣኔን ለማጠናከር በትኩረት እንሰራለን - ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ወግና ባህል የተቃኘ፣ ከዓለም እኩል መራመድ የሚያስችል ትምህርት፣ ቴክኖሎጂና ሥልጣኔ ለማጠናከር በትኩረት እንሰራለን ሲሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበረ ይገኛል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በ75 ዓመታት ጉዞው ከ300 ሺህ በላይ ምሩቃንን በማፍራት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ የራሱን አሻራ አሳርፏል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ከሀገር መሪዎች እስከ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችን ያፈራ የሀገር ባለውለታ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ የተሳለጠ የውጭና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መንገድ አሳይቷል፤ ለግብርናና አካባቢ ጥበቃ ስራዎች ሀሳብ አዋጥቷል፣ ለትምህርትና ስልጠና ስርዓት መሻሻል መሰረት ጥሏል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው 75ኛ ዓመት በዓል ሲከበር ስራዎችን ለመዘከርና ታረክ ለመንገር ብቻ አይደለም ያሉት ሳሙኤል (ዶ/ር)፤ ለሀገራዊ ብልጽግና አጋዥ ሀሳቦችን ለማለም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ፤ የ75ኛ ዓመት ምስረታ በዓልና የራስ ገዝነት አስተዳደር የተገናኙበትን የታሪክ ግጥምጥሞሽም የቀጣይ ሥራዎችን በፍጥነትና በጥራት ለመስራት መልካም ዕድል የፈጠረ ብለውታል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በራስ ገዝነት ያገኘውን ወርቃማ ዕድል በመጠቀም ለኢትዮጵያ ብልጽግና ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ዩኒቨርሲቲው ያገኘውን የራስ ገዝነት ዕድልም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመጥርና ለኢትዮጵያና ህዝቦች ዕድገት ገንቢ ሚና የሚወጣ ተቋም እንዲሆን ያስችለዋል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በሀገራዊ ወግና ባህል የተቃኘ፣ ከዓለም እኩል መራመድ የሚያስችል ትምህርት፣ ቴክኖሎጂና ሥልጣኔ ሊኖራት ይገባል ያሉት ሳሙኤል (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው ለዚህ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የቀጣዩ ዘመን የመወዳደሪያ መድረክ መሆኑን ገልጸው፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ፕሮግራሙን በሶስተኛ ዲግሪ ደረጃ ማስተማር ጀምሯል ብለዋል፡፡

ይሄውም የመንግስት የፖሊሲ አቅጣጫዎች ማሳካትና ኢትዮጵያ በነባራዊው ዓለም ተወዳዳሪ የምትሆንበትን አውድ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ለመለወጥ በምታደርገው ጥረት በጥናትና ምርምር የታገዘ ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣቱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም