ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን ገለጹ።

በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለአምስት ተከታታይ ቀናት የተካሄደው ሁለተኛው የብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ(ግሪን ሞቢሊቲ) አውደ ርዕይና ፎረም 2025 ተጠናቋል።

በአውደ ርዕይና ፎረሙ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን፤ የዘንድሮው ዓውደ ርዕይ ዓላማውን ያሳካና ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተካሄዱ የውይይት መድረኮችም በርካታ አካላትን ያገናኙና ውጤታማ መረጃዎች የተለዋወጡባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በአውደ ርዕዩ ኢትዮጵያውያን በዘርፉ ላይ የላቁ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራዎችን በማቅረብ ሻጮችና ሸማቾች የተገናኙበት ትልቅ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።


 

መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ ብሩህ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ሀገሪቱ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ዘርፍ የጀመረቻቸውን ውጤታማ ሥራዎች አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በዓውደ ርዕዩ አዳዲስ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ቴክኖሎጂዎች ለዕይታ መቅረባቸውንና ዘርፉ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ያለውን ፋይዳ በተመለከተም የጋራ ግንዛቤ የተፈጠረበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ለአውደ ርዕዩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ ተሳታፊዎች ምስጋና አቅርበው፤ በመጪው ዘመን በፈጠራው ዘርፍ የተሻሉ ሥራዎች እንደሚጠበቁም አመልክተዋል።

ዓውደ ርዕዩ በቀጣይም ይበልጥ እንዲሳካ በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ተጋላጭነት ለመውጣት የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስፋፋት በኩል ውጤታማ የአረንጓዴ ልማት እርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝም በዚሁ ወቅት ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም