ቀጥታ፡

በከተማው ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እያገዘ ነው

ጎንደር፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ በጎንደር ከተማ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የዜጎችን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በመፍታት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ምህዳር እየፈጠረ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ተናገሩ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ መሬት መምሪያ ዘመናዊ የመሬት ይዞታ መረጃን በዲጂታል የመረጃ ስርዓት መምራት የሚያስችለውን የካዳስተር አሰራር በይፋ በማስመረቅ ዛሬ አስጀምሯል፡፡

በምረቃው የተገኙት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው እንደተናገሩት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ኢንሼቲቭ ከተሞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የዲጂታል አገልግሎት እንዲሰጡ መሰረት የጣለ ነው።


 

ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዜጎች ማናቸውንም የመንግስት አገልግሎቶች ፈጣንና ቀልጣፋ በሆነ መልኩ እንዲያገኙ አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

ገቢ የመሰብሰብ አቅምን በማሳደግ ልማትና እድገትን ለማፋጠን አዎንታዊ ሚና እንዳለውም ነው የተናገሩት፡፡

የመሬት ይዞታ መረጃ ስርዓቱ ዲጂታል መደረጉ በከተማዋ ህገ ወጥ ግንባታንና የመሬት ወረራን ለመቆጣጠር ብሎም በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡


 

የካዳስተር ሥርዓት የከተማውን የመሬት ሀብት በአግባቡ ቆጥሮና ለይቶ በማደራጀት አልምቶ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ መሬት መምሪያ ሃላፊ ትዛዙ በጽሃ ናቸው፡፡

የካዳስተር ስርዓት በተተገበረባቸው ከ2010 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት ከ21ሺህ በላይ የመሬት ይዞታዎችን የመለየትና መረጃ የማሰባሰብ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ ታግዞ ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመትም ከ15ሺህ በላይ ይዞታዎችን መረጃ ማሰባሰቡን ገልጸው፣ ሁሉንም ይዞታዎች ወደ መረጃ ቋት በማስገባት በአሁኑ ወቅት ይዞታቸው ለተረጋገጠላቸው ነዋሪዎች ዲጂታል ካርታ የመስጠት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በዛሬው እለት ዲጂታል ካርታ ከተረከቡ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሃና ማለደ በሰጡት አስተያየት ዲጂታል ካርታ ዜጎች አስተማማኝ የይዞታ ማረጋገጫ አንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡


 

ዲጂታል ካርታ ከዚህ ቀደም በመሬት ይዞታ ይረጋገጥልኝ ጥያቄ ላይ ያጋጥሙ የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን የሚያስቀርና ከእንግልት የሚታደግ በመሆኑ መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ አህመድ ለጋስ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም