የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዓለም አቀፍ የግብይት ተወዳዳሪነትን በማስፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዓለም አቀፍ የግብይት ተወዳዳሪነትን በማስፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዓለም አቀፍ የግብይት ተወዳዳሪነትን በማስፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚጠበቅበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው ከ2014 እስከ 2016 ዓ.ም ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምርት ቅበላ፣ ክምችና የግብይት ስርዓት ላይ የተካሔደ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።
በክዋኔ ኦዲት እንደክፍተት ከታዩ ጉዳዮች መካከል የምርት አቀባበል ሂደት እና ዘመናዊ የግብይት አሰራር መፍጠር ላይ የተነሱ ጉድለቶች ተጠቃሽ ናቸው።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አራሬ ሞሲሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ምርት ገበያው በክዋኔ ኦዲት ግኝት የተቀመጡ ክፍተቶችን በማስተካከል የተሰጠውን ኃላፊነት በሚገባ መወጣት ይኖርበታል።
በተለይም በመጋዘን ኪራይና ግንባታ ላይ በቋሚ ኮሚቴው የተሰጠውን የክዋኔ ኦዲት አስተያየት በማስተካከል የአርሶ አደሩንና የሀገርን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተነደፈው የምርት ቅበላ፣ ግብይትና ክምችት የድርጊት መርሃ ግብር ተፈፃሚነትም በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሀኪም ሙሉ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በምርት ገበያው የተስተዋሉ የኦዲት ግኝቶች ላይ የተቀናጀ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያሻሽል ወቅታዊ መረጃዎችን በመስጠት ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ግኝት ጭምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እየበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀደም ብሎ በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ የኦዲት ግኝት አስተያየቶችን ተከትሎ በተወሰዱ እርምጃዎች በሰው ሃብት ልማትና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ስኬታማ ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ፤ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመጋዘን አያያዝና ዘመናዊ ግብይት አሰራሮች ላይ የተሰጡትን የኦዲት ግኝቶች ለማስተካከል በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በቀጣይም በምርት ገበያው የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች ላይ አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪነትን ማሻሻል እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መርጋ በይሳ በበኩላቸው፤ ቋሚ ኮሚቴው በምርት ገበያው በሰጠው የክዋኔ ኦዲት ክፍተት አስተያየት ላይ የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።
በዚህም ነባርና አዳዲስ ምርቶችን ከምርት ገበያው ጋር በማሰናሰል አርሶ አደሮች በቀጥታ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በቀጣይም በዋና ኦዲተር የተመላከቱ የክዋኔ ኦዲት ግኝቶችን በማስተካከል ዓለም አቀፍ የምርት ገበያ ተወዳዳሪነትን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።