ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር የምታከናውናቸው ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት ለጋራ ልማትና ዕድገት ወሳኝ ሚና አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር የምታከናውናቸው ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት ለጋራ ልማትና ዕድገት ወሳኝ ሚና አላቸው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር የምታከናውናቸው ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት ለጋራ ልማትና ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን ገለጹ።
ምሁራኑ ቀጣናዊ ትስስር መፈጠር የንግድ ፍሰቱን ከማሳለጥ ባለፈ ለዘላቂ ሰላምና ለሁለንተናዊ እድገት መሰረት በመሆኑ በጋራ የመልማት አስፈላጊነትን ጉልህ ያደርገዋል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም እና ገቨርናንስ መምህርና ተመራማሪ ተስፋዬ ጂማ(ዶ/ር)፤ የቀይ ባህር ቀጣና የዓለም ኃያላን መንግስታት ስትራቴጂካዊ የፍላጎት ማዕከል እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ካለው ጂኦስትራቴጂክ ጠቀሜታ ባለፈ ለኢንዱስትሪ ዕድገት፣ ለቱሪዝም፣ ለባህል ልውውጥና ለግዙፍ የንግድ እንቅስቃሴዎች ምቹ መሆኑን አብራርተዋል።
የቀጣናው ሀገራት ቀይ ባህርን በጋራ ማልማትና መጠቀም የሚያስችል ትብብር መፍጠር ከቻሉ ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም የመገንባት ዕድላቸውም ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም በቀጣናው የሚከናወኑ የወደብና ሎጂስቲክ መሰረተ ልማት ግንባታዎች በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ ለቀጣናው ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት አዎንታዊ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ሰላማዊና በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ የትብብር ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት በቀይ ባህር ያላት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ማድረግ ለጋራ ብልጽግና እውን መሆን ከፍተኛ ድርሻ አለው ነው ያሉት።
በቀጣናው የጋራ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር የሚፈጥር ተቋም መገንባት ወሳኝ መሆኑን አንስተው የቀይ ባህር አካባቢን ማልማትና መጠቀም ከሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦ ፖለቲካዊ ጥቅሞች አኳያ ከተናጠል እንቅስቃሴ ይልቅ በጋራ መስራት የቀጣናው ሀገራት ቁልፍ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባም መክረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሰላምና ደኅንነት ተመራማሪው ሙሉጌታ አየለ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የሌሎች ሀገራትን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም የምታከብር መሆኗን ተናግረዋል።
በጎረቤት ሀገራት መሪዎችና በሥርዓት ለውጥ የማይበገር ጠንካራ የሉዓላዊነት አቋም በተግባር ስታሳይ መቆየቷን ጠቁመውይህንኑ ታሪካዊ እውነት ከአፍሪካ ሕብረት ምስረታ ጀምሮ ያስመሰከረች ሀገር መሆኗን አስታውሰዋል።