ጥልቅ ንባቡን እና የሀገር ፍቅሩን በስራዎቹ የገለጠ የጥበብ ሰው - ያየህይራድ አላምረው - ኢዜአ አማርኛ
ጥልቅ ንባቡን እና የሀገር ፍቅሩን በስራዎቹ የገለጠ የጥበብ ሰው - ያየህይራድ አላምረው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ የሁለገቡ የጥበብ ሰው ያየህይራድ አላምረው የመፃሕፍት፣ መዛግብትና የጥበብ ስራ ስብስቦች ለኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ተበርክተዋል።
የተበረከቱ የመዛግብት፣ የመጻሕፍትና የጥብብ ስራ ስብስቦች ‘የአርቲስት ያየህይራድ አላምረው መዘክርና የስብስቦቹ ቤተ መፃሕፍት’ በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ውስጥ ተደራጅተው ክፍት ተደርገዋል።
ሀገር ተኮር በሆኑ የዘፈን ግጥሞችና ዜማዎች ደራሲነቱ እንዲሁም በፕሮዲዩሰርነት የሚታወቀው ያየህይራድ አላምረው ባሳለፍነው ዓመት ታህሳስ ወር ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው።
በንባብ ወዳድነቱና መዛግብት ሰብሳቢነቱ የሚታወቀው አርቲስቱ በሕይወት ዘመኑ ያሰባሰባቸውን ከ5 ሺህ በላይ መፃሕፍት፣ መዛግብትና የጥበብ ስራ ውጤት የሆኑ ስብስቦች በቤተሰቦቹ በኩል ለኢትዮጵያ ቤተ መፃሕፍት አገልግሎት ተበርክተዋል።
በኢትዮጵያ የቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የተደራጀው የያየህይራድ ስብስቦች ቤተ መፃሕፍት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ(ረ/ፕ)ን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ የአርቲስቱ ቤተሰቦችና ወዳጆቹ በተገኙበት ዛሬ ይፋ ተደርጓል።
ሚኒስትር ዴኤታው ነብዩ ባዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት ያየህይራድ አላምረው በንባብ የተገራና የለሰለሰ፣ አስተዋይ እና ፈገግታ የማይለየው የመልካም ስብዕና ባለቤት የጥበብ ሰው ነበር።
ያየህይራድ በጥልቅ አንባቢነቱና ከቤተሰብ የወረሰውን የኢትዮጵያ አፍቃሪነቱን በጥበብ ስራዎቹ የገለጠ ድንቅ ባለሙያ እንደሆነ ገልፀዋል።
በሕይወት ዘመኑ ያሰባሰባቸው መፃሕፍት እና ሌሎች ስብስቦች ለትውልድ እንዲተርፉ ለአንጋፋው ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት አገልግሎት ተደራጅተው እንዲያቀርቡ ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር እና የያየይራድ የቅርብ ጓደኛ የሆኑት ጌታቸው ረዳ ያየህይራድ አላምረው ማንበብ የሚወድ፣ ሃሳቡን በቀላሉ መግለጽ የሚችል እና ለሁሉም ጓደኛ መሆን የሚችል የዋህ ሰው እንደነበር ተናግረዋል።
የአርቲስቱ የመፃሕፍትና የጥበብ ስራዎች ውጤቶች በዚህ መልኩ ተደራጀተው ለታሪክ መቀመጣቸው ትልቅ ቁምነገር ስለመሆኑም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰርፀፍሬ ስብሃት በበኩላቸው ያየህይራድ ብዙ ያወቀ ዳሩ በስራዎቹ ጥልቀት ልክ በቅጡ ያልታወቀና ያልተነገረለት የጥበብ ሰው መሆኑን ገልጸዋል።
ለአገልግሎቱ የተበረከቱ ስብሰቦች ይዘትና አይነት እጅግ አስደናቂ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ያየህይራድ አንባቢነትና የሀገር ፍቅር ለኪነ ጥበብ ሰዎች በተምሳሌትነት የሚወሰድ ነው ብለዋል።
አርቲስቱ በጥበብ ስራዎቹ ያሳየውን የሃሳብ ገለፃ፣ የቃላት አጠቃቀምና የመልዕክቱን ጥልቀት አንስተዋል።
‘ከይቺ ናት ሀገሬ እስከ ቁሜ ልመርቅሽ’ አያሌ የኢትዮጵያ ዕውቅ ሙዚቀኞች ተወዳጅ ዘፈኖች የያየህይራድ አላምረው አሻራዎች ማሳያ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በያየህይራድ ‘አንጀት አርስ’ ብዕር መገለጧን ጠቅሰው፤ አሁን ደግሞ የያየህይራድ ስብስቦች በአገልግሎቱ ውስጥ ተደራጅተው ለኢትዮጵያ ተገልጠዋል ነው ያሉት።
አንጋፋው የኢትዮጵያ ቤተ መዛግበትና ቤተ መፃሕፍት አገልግሎት ኢትዮጵያን ለማወቅ እና መዛግብትን ለትውልድ ለማሻገር ሁናኘ ስፍራ መሆኑን በመጥቅስ የጥበብ ሰዎችም ይህን አርዓያነት እንዲከተሉ ጠይቀዋል።
በመድረኩ ላይ ሃሳባቸውን የሰጡት የአርቲስቱ ቤተሰቦችና ወዳጆችም ያየህይራድ በሀገር ፍቅር ስሜት፣ በጥልቅ አንባቢነትና በጥበብ ስራዎች ረቂቅነቱን ገልጸዋል።