አርሶ አደሮች ቡናን በጥራት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ያላቸው ተነሳሽነት እያደገ መጥቷል - ሚኒስትር አዲሱ አረጋ - ኢዜአ አማርኛ
አርሶ አደሮች ቡናን በጥራት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ያላቸው ተነሳሽነት እያደገ መጥቷል - ሚኒስትር አዲሱ አረጋ
ሀዋሳ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ በሁሉም ቡና አብቃይ ወረዳዎች በተደረገ የባለሙያ ድጋፍ አርሶ አደሮች ቡናን በጥራት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ያላቸው ተነሳሽነት እየተሻሻለ መምጣቱን የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ ገለጹ።
በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ በቡና ልማት ላይ የተሳተፉ አርሶ አደር ማሳ የጎበኙት የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ እንዳሉት በተያዘው ዓመት 600ሺህ ቶን ቡና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ታቅዷል።
ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው የቡና ምርት ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ግብ ተይዞ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በሲዳማ ክልሉ ቡና አምራች በሆኑ አካባቢዎች የቡና ጥራትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚ ለመሆን እየተሰራ ያለው ሥራ በዘርፉ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።
የቡና ዝርያን ለማሻሻል፣ የአመራረት ዘዴን ለማዘመን፣ ኩታ ገጠም የቡና ልማትን ለማስፋፋትና ምርታማነታቸው የተረጋገጠ የቡና ዝርያዎችን ለማልማት የተሰራው ሥራ ዕቅዱን ለማሳካት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ቡና በቻይና የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በተለይ ከባለ ልዩ ጣዕም ቡና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በቀጣይ በተለያዩ ሀገራት የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል ብለዋል።
ዘንድሮ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እንዳሉ ጠቁመው፣ በሁሉም ቡና አብቃይ ወረዳዎች በተደረገ የባለሙያ ድጋፍ አርሶ አደሮች ቡናን በጥራት አምርቶ ለማቅረብ ያላቸው ተነሳሽነት መሻሻሉን ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው በክልሉ ቡና እና አቮካዶ ለውጪ ገበያ እንደሚቀርብ ታሳቢ ተደርጎ እየሰተራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመጠቀም የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማሻሻል ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው አዳዲስ የቡና ዝርያዎችን መጠቀምን ጨምሮ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በእርጅና ምክንያት ምርታማነቱ የቀነሰ የቡና ተክልን በአዲስ የመተካትና ባህር ዛፍን ነቅሎ በቡና የመተካት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
የክልሉ ቡና፣ ቅመማቅመምና ፍራፍሬ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ቃሬ በክልሉ በተያዘው ዓመት ወደ ውጪ ከሚላከው 40ሺህ ቶን ቡና 17 በመቶ የሚሆነው ባለልዩ ጣዕም እንደሚሆንና ይህንንም በሂደት ወደ 20 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አርሶ አደሮችም ባለልዩ ጣዕም ቡና አምርተው ለውጪ ገበያ በራሳቸው በቀጥታ መላክ እንዲችሉ ለ400 አርሶ አደሮች ፈቃድ በመስጠት ክትትልና ደጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
በክልሉ ሸበዲኖ ወረዳ ባለልዩ ጣዕም ቡና አምርተው ለውጪ ገበያ ቀጥታ ለማቅረብ ፈቃድ ከተሰጣቸው አርሶ አደሮች መካከል ቦዳ ሳጉና እንዳሉት በሁለት ሄክታር መሬት ቡና እንዳለሙና ከሄክታር 30 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
ያመረቱትን ምርት በቀጥታ ወደ ውጪ ለመላክ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ እና ከቡና፣ ቅመማቅመምና ፍራፍሬ ባለስልጣን ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።