የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የመዲናዋን የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት ለማላቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የመዲናዋን የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት ለማላቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የመዲናዋን የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማላቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ስኬታማነት የማጠናቀቂያና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ማብሰሪያ መርሃግብር መካሄዱ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅትም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል ዕድል መፍጠር፣ የዜጎችና ተቋማትን መተማመን ማጎልበት ቁልፍ ትልሞች መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን የሚያሳልጥ መሰረት ተጥሏል።
የዲጂታል ዓለም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የፈጠረው ከፍተኛ አቅም ለኢንዱስትሪ የምርት ጥራትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት መልካም አጋጣሚዎችን እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ሥርዓትም ለመዲናዋ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ቁጥርና የምርታማነት አቅም በማላቅ ወሳኝ ሚና እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማም ከ3 ሺህ 824 በላይ ኢንዱስትሪዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት የታገዘ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለገበያ በመቅረብ እመርታዊ ለውጥ እያመጡ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበረው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ቁልፍ ትልሞችም የኢንዱስትሪ ምርታማነትን በማላቅ ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ የውድድር መድረክ እየሆነ በመጣው የዲጂታላይዜሽን ሥርዓት ውስጥ መሪ ተዋናይ ለመሆን ዘመኑ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ውጤት መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም በአዲስ አበባና በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለተሰማሩ አልሚዎች ምርታማነት ወሳኝ አቅም እንደሚፈጥር አንስተዋል።