የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ድርሻ እንዲይዝ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ድርሻ እንዲይዝ አስችሏል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ድርሻ እንዲይዝ ማስቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት እያሻሻለ የሚገኝ ስልታዊ የስትራቴጂክ ትልም መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ታምርት ሀገር አቀፍ ንቅናቄም አምራች ኢንዱስትሪ የማምረት አቅም በማሳደግ በተኪና ወጪ ምርት እንዲሁም በዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል።
በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ ውጤቶች፣ በምግብና መጠጥ የግብርና ማቀነባበር፣ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ማምረት የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን ስኬታማነት አሳድጓል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪ ዕድገትን የሚያሳልጥ ምቹ የፖሊሲና የአሰራር ምኅዳር መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚነሱ ማነቆዎችን መፍትሔ ለመስጠት የተከናወኑ ተግባራት የዘርፉን ምርታማነት ከ45 በመቶ ወደ 65 በመቶ ማሳደግ ያስቻለ እመርታ መገኘቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከመጀመሩ በፊት ለሀገር ውስጥ ገበያ ይቀርብ የነበረን ከ340 ሚሊየን ዶላር የማይበልጥ ምርት አሁን ላይ ወደ 4 ቢሊየን ዶላር ማሳደግ እንደተቻለ አስረድተዋል።
በሂደቱም በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የተፈጠረው መነቃቃት አዳዲስ የሀገር ውስጥና የውጭ አምራቾች በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳለጥ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ መምሪያ ኃላፊ ብርሃን ንጉሴ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 45 ኢንዱስትሪዎች በባሕር ዳር ከተማ እንዲሰማሩ አስችሏል ብለዋል፡፡
ንቅናቄውም አምራቾች የልምድ ልውውጥና የቴክኖሎጂ ትስስር እንዲፈጥሩ በማስቻል የጋራ ችግሮቻቸውን በተቀናጀ የአሰራር ሥርዓት መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።