የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሁሉም በጋራ ጸንቶ የሚቆምለት የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሁሉም በጋራ ጸንቶ የሚቆምለት የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሀገርን ታላቅነት የሚወስንና ሁሉም በጋራ ጸንቶ የሚቆምለት የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ ነው ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የሀገርን የመልማት ፍላጎት በሁሉም አካባቢዎች በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ዜጎች እያበረከቱ ያሉትን ጉልህ አስተዋጽኦ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
ኢትዮጵያውያን በጋራ ብሔራዊ ጥቅማቸው ላይ ጸንተው መቆም እንደሚገባቸው ጠቁመው፤ ለዚህም የሀገሪቷን ሰላምና ደህንነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የመደመር መንግስት ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት እሴቶች ጎልብተው እንዲወጡና ለሀገር ግንባታ ምሰሶ እንዲሆኑ በትጋት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ሁሉም ወገኖች ለልማት መረጋገጥና ለዜጎች ብልጽግና በአንድነት መቆም እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
የባህር በር ባለቤትነትን በተመለከተ ኢትዮጵያ የምታነሳው ጥያቄ በቂና አሳማኝ ምክንያቶች ያሉት መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ዋና ዋናዎቹም ታሪካዊ፣ መልክአ ምድራዊ ምክንያቶች፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሕጋዊ መሠረቶች፣ የጸጥታና የደህንነት ጉዳዮች ጋር የሚገናኙ ናቸው ብለዋል፡፡
የባህር በር ጥያቄ የወደብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ትልቅነት የሚወስን ነው ያሉት ተጠሪ ሚኒስትሩ፤ ቀደም ባሉት ሥርዓቶች ይህንን ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች ጦረኛና ሀገር አተራማሽ አድርጎ መቁጠር ስህተት እንደነበር አስታውሰዋል።
ዛሬም ይህንን የተሳሳተ ትርክት የሚደግሙ አካላት እንዳሉ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ጥያቄው በመነሳቱ ጋርዶ የቆየው መጋረጃ መቀደዱን ገልጸዋል።
በቅርቡ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተደረገው ውይይት፣ የባህር በር ጥያቄው ሰፊ የሕዝብ መሠረት ያለው መሆኑ መረጋገጡን ጠቁመው፤ ጥቂት ታሪካዊ ጠላቶች ካልሆኑ በስተቀር አብዛኛው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የጥያቄውን ፍትሃዊነት እየተረዳ መምጣቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በውኃ ሀብቷ እንዳትጠቀምና ከውኃ አካላት እንድትርቅ የተደራጀ ሴራ ሲሰራባት መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የኢትዮጵያ ጠላቶች መሣሪያ የሚሆኑ ጥቂት ግለሰቦች ከታሪክ ሊማሩ ይገባል ብለዋል።
የሀገረ መንግስት ግንባታ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮችና በብሔራዊ ጥቅሞች ዙሪያ ሁሉም ዜጎች ወጥ የሆነ አቋም ሊኖራቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።