የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቀጣይ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ምንድን ናቸው? - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቀጣይ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ምንድን ናቸው?
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ኮሚሽኑ በቀጣይ የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራትንም አብራርተዋል።
በዚህም ኮሚሽኑ ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ከመጥራቱ በፊት መከናወን ያለባቸው ዋና ዋና ተግባራት መኖራቸውን አስታውቀዋል።
ከእነዚህም መካከል አሁን ጥረቶች እየተደረጉበት ያለውና ትግራይ ክልልን በምክክር ሂደቱ ማሳተፍ አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኮሚሽኑ ዕቅድ መሠረትም ክልሉ በቅርቡ እንደሌሎቹ ክልሎች ተሳታፊዎችን በመለየት አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የትግራይ ክልል አጀንዳ ከተሰበሰበ በኋላ ሌላው ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራው ሥራ አጀንዳ መቅረጽ መሆኑንም አመላክተዋል።
እስካሁን በርካታ አጀንዳዎች መሰብሰባቸውን ገልጸው፤ ከእነዚህ አጀንዳዎች መካከል ለምክክር ጉባዔው የሚቀርቡት መሠረታዊና ሀገራዊ አጀንዳዎች ይለያሉ ብለዋል።
አክለውም፤ ለሀገራዊ ምክክሩ ባይቀርቡም በየደረጃው ትኩረት የሚያስፈልጋቸው አጀንዳዎች የትኞቹ እንደሆኑ የመለየት ተግባር እንደሚከናወንም አስገንዝበዋል።
ሀገራዊ ምክክር የሚደረግባቸው አጀንዳዎችን ለሕዝቡና ለባለድርሻ አካላት ይፋ ማድረግና የአጀንዳ ቀረጻ ማከናወን ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ያለ ተግባር ስለመሆኑም አንስተዋል።
ሂደቱ አሳታፊና አካታች እንዲሆን በተከናወኑ ተግባራት በርካቶች እየተሳተፉ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ እስካሁን ወደ በሂደቱ ያልተሳተፉ አካላት እንዲሳተፉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት በተለይም በሂደቱ እየተሳተፉ ያልሆኑ አካላትን ወደ ሂደቱ ለማምጣት ኮሚሽኑ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራባቸዋል ነው ያሉት።
ከላይ የተገለጹትና ተያያዥ ተግባራት ተከናውነው ሲጠናቀቁ፤ መጨረሻ ላይ የሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክሩን የመጥራት ጉዳይ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለጉባዔው በሚቀረጹ አጀንዳዎች ላይ ምክክር በማድረግ መግባባት ላይ መድረስ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ በማቋቋሚያ ዐዋጁ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት ምክክር ተደርጎ መግባባት የሚደረስባቸውን ጉዳዮች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ምክረ ሐሳብ በመዘጋጀት ለሚመለከታቸው በማቅረብ አፈጻጸሙን የመከታተልና የማገዝ ሥራዎች ይሠራል ብለዋል።