የአገው ፈረሰኞች በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
የአገው ፈረሰኞች በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተከናውኗል
ባህርዳር ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦የአገው ፈረሰኞች በዓልን በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን መሀመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
በዓሉን በመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ የሰው ልጆች ወካይ ባህላዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ በሚያስችለው የመጨረሻ ሰነድ ላይ የውይይት መድረክ በባህር ዳር እየተካሄደ ነው።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን መሀመድ(ዶ/ር) ፤ በክልሉ የቱሪዝም ሃብትን በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በፌደራል መንግስት የፋሲል አብያተ መንግስታትንና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጥገና ከማድረግ ጎን ለጎን እንደ ጎርጎራ ያሉ አዳዲስ መዳረሻዎችም መልማታቸውን ለአብነት አንስተዋል።
ተግባሩን በማስቀጠልም የአገው ፈረሰኞች በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ጋር በመሆን በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።
የክልሉ መንግስትም ቅርሱን ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዓሉ የዓድዋ ድል ታሪክ የወለደው የታታሪነትና የአይበገሬነት መገለጫ ነው ብለዋል።
በዓሉ በውስጡ ጥበብ፣ ህብረብሔራዊነት፣ የጋራ ድልና የኢትዮጵያ እሴትን የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ለአንድ ዞን ወይም ክልል ብቻ የሚተው ሳይሆን የሀገር ሃብት ነው ብለዋል።
ይህንን ትልቅ የሀገር ሃብት በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት ሁሉ የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደገለጹት፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት የሀገር ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ስራ ላይ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል።
የአገው ፈረሰኞችን በዓል በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችለው የመጨረሻው ሰነድ ላይ መድረስ መቻሉም መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ፤ በዓሉ በዓለም ቅርስነት ይመዝገብልን የሚለው የህዝብ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ጫፍ ደርሷል ብለዋል።
ቢሮውም ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲና ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በዓሉ በዩኔስኮ ቅርስነት እንዲመዘገብ መስራቱን ጠቁመው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣንም እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ቴዎድሮስ እንዳለው በበኩላቸው፤የአገው ፈረሰኞች በዓል በቀጣይ ጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም 86ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ያከብራል ብለዋል።
በመድረኩ ላይም የክልል፣ የፌደራልና የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ የዘርፉ ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።