በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሁሉም ሆስፒታሎች የዲጂታል የጤና አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሁሉም ሆስፒታሎች የዲጂታል የጤና አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሁሉም ሆስፒታሎች የጤና አገልግሎቶችን በዲጂታል መስጠት የሚችሉባቸው ግብዓቶች እየተሟሉ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ የዜጎችን ጤናና ማህበራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍና ሀገራዊ የጤና ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ገቢራዊ አድርጋለች፡፡
በዚህም መከላከልን መሰረተ ባደረገው የጤና ፖሊሲዋ የእናቶችና ህፃናትን ሞት በመቀነስ በዘላቂ የልማት ግቦች የተቀመጡ ዕቅዶችን ቀድማ ማሳካት ችላለች፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ የጤና ተቋማትን በግብዓት በማዘመን፣ በዲጂታል የታገዘ የጤና አገልግሎት በመስጠት ዲጂታል ቴክኖሎጂን በተሻለ የሚጠቀም ተቋም ነው፡፡
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ለጤናው ዘርፍ መልካም ዕድል ይዞ መምጣቱን ገልጸው፤ በስትራቴጂው ማብቂያ አብዛኞቹ የጤና ተቋማት የመረጃ ስልታቸውን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ያስገባሉ ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በ2030 ሁሉም ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ ወረቀት አልባ አገልግሎት እንዲሰጡ አስፈላጊው የዲጂታል አገልግሎት ግብዓት እየተሟላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና ሥርዓት በቀበሌዎች ያለውን መረጃ በዲጂታል ሥርዓት ይዘው ሪፖርት የሚያደርጉበት አሰራር መኖሩንም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ይህንን አሰራር ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ በማድረግ የዲጂታል አገልግሎት በጤናው ዘርፍ የላቀ አገልግሎት እንዲኖረው ይደረጋል ብለዋል፡፡
የጤና ተቋማትን ማዕከል ያደረጉ የመረጃ ሥርዓቶች ወደ ዲጂታል ይገባሉ ያሉት ዶክተር ደረጀ፤ የጤና ባለሙያዎች ላይ ቁጥጥር የሚደረግበት አሰራር ገቢራዊ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዜጎች ከቤታቸው ሆነው የጤና ምክርና አገልግሎት የሚያገኙበትን፣ ቀጠሮ የሚይዙበትን ቀላልና ቀልጣፋ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የታካሚዎች የህክምና መረጃ በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል የዲጂታል ስርዓት ገቢራዊ እንደሚደረግ በመጥቀስ፤የዲጂታል መረጃ ስርዓቱን የሚያሳልጡ ግብዓቶች ወደ ሀገር ቤት እየገቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡