የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ትኩረት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 22/2018(ኢዜአ)፦ የዜጎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት ትኩረት መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ።
አገልግሎቱ እንዳስታወቀው፤ በርካታ ሕብረተሰብ ለሚኖርባቸው አካባቢዎች በሰጠው ትኩረት መሰረት በአዲስ አበባ የጨፌ ቡልቡላ ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎችን የ24 ሠዓት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
በአንድ ወር ውስጥ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ዝርጋታ በማጠናቀቅ ነዋሪዎቹን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት በጨፌ ቡልቡላ ኮንዶሚኒየም በ23 ብሎኮች የሚኖሩ 575 ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ለኢዜአ አረጋግጠዋል።
የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎቹን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ አንድ ኪሎ ሜትር የመካከለኛና አንድ ነጥብ አንድ ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ የመሬት ውስጥ ተቀባሪ መስመር ዝርጋታ መከናወኑንም አስረድተዋል።
በተጨማሪም 4 ባለ 630 ኪሎ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች ተከላ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ በተናጠል ተጠቃሚ ከመሆናቸው በፊት ባለ ሦስት ፌዝ ቆጣሪ በጋራ ይጠቀሙ እንደነበር ነው ያስታወሱት።
ተጠቃሚዎች በበኩላቸው ላለፉት አምስት ዓመታት እንጀራ ለመጋገርም ሆነ ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት ይቸገሩ እንደነበር አውስተዋል።
በዚህም በኃይል መቆራረጥና በኃይል ማነስ ምክንያት ለረዥም ጊዜ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ አሁን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ በመሆናቸው ችግራቸው መቀረፉን ተናግረዋል።