በመሪዎች መካከል የተደረጉ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመሪዎች መካከል የተደረጉ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያና ህንድ መሪዎች መካከል የተደረጉ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እና የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂክ አጋርነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ገለፁ።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት ማደጉ ከኢኮኖሚና ንግድ ባለፈ ያላቸውን የትብብር አድማስ የሚያሰፋ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፤ኢትዮጵያና ህንድ ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።
ኢትዮጵያ በህንድ የባህል ማዕከል ያላት ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗን አንስተው፤ የኢትዮጵያን ባህል በህንድ የበለጠ ለማስተዋወቅ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት ከ40 በላይ በረራ ወደ ህንድ እንደሚያደርግ የገለጹት አምባሳደሩ ተቋሙን የኢትዮጵያ የባህል አምባሳደር ሲሉ አሞካሽተውታል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሪንድራ ሞዲ ጉብኝትን ተከትሎ የህንድና ኢትዮጵያ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት ማደጉንም አስታውሰዋል።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት ማደጉ ከኢኮኖሚና ንግድ ባለፈ የትብብር አድማስን የሚያሰፋ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጉብኝቱን ተከትሎ ሀገራቱ በጉምሩክ፣ በሰላም ማስከበር፣ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳታ ማዕከል መገንባትን ጨምሮ የተለያዩ ስምምነቶች መፈራረማቸውንም አስታውሰዋል።
የሀገራቱ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት ማደግ የደቡብ ለደቡብ ትብብርን የሚያጠናክርና ሀገራቱ ያላቸውን ዓለም አቀፍ አጋርነት የሚያጎለብት መሆኑን አስረድተዋል።
በህንድ የትምህርት እድል የሚያገኙ ኢትዮጵያውያንን ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ ስምምነት ላይ መደረሱንም አንስተዋል።
ሀገራቱ በጋራ ለመስራት የተስማሙባቸውን ተግባራት ለማስፈፀምና ስትራቴጂክ አጋርነቱን ለማጠናከር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።