የተከናወኑ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራዎች ምርታማነትን አሳድገዋል - ኢዜአ አማርኛ
የተከናወኑ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራዎች ምርታማነትን አሳድገዋል
አዲስ አበባ፣ታኅሣስ 22/2018 (ኢዜአ)፡-ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራዎች ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻላቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ገልጿል።
የቢሮው ምክትልና የተፈጥሮ ሐብት ዘርፍ ኃላፊ አብዱልከሪም ሙሳ እንዳሉት፤የዘንድሮው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ የፊታችን ጥር ወር ይጀመራል።
በሁሉም ወረዳዎች በሚከናወነው ሥራም በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት ከ57 ሺህ ሔክታር በሚልቅ መሬት ላይ የአፈርና ውኃ ዕቀባ ሥራ ለማከናወን መታቀዱን ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት በ52 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ መከናወኑንም አውስተዋል።
ቀደም ባሉት ዓመታት የተከናወኑ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራዎች በርካታ ጥቅሞች ማስገኘታቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ከእነዚህ ጥቅሞች መካከል የምርትና ምርታማነት መጨመር፣ የአፈር መሸርሸር መቀነስ፣ የምንጮች መጎልበትና የመስኖ ተጠቃሚነት ማደግ የሚሉትን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ የሚያስገኘውን ዘርፈ-ብዙ ተጠቃሚነት በመገንዘብ በጥር ወር በሚጀመረው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ሕብረተሰቡ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።