ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፖስታ አዳዲስ መተግበሪያዎች አሰራሩን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፖስታ አዳዲስ መተግበሪያዎች የዲጂታል ኢትዮጵያን ስትራቴጂ ወደ ተግባር የሚቀይሩና አሰራሩን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

ዛሬ “የሳጥን አልባ የመልዕክት አገልግሎት”(Virtual post Box) እና “የፖስታ ገበያ” የተሰኙ አዳዲስ መተግበሪያዎች ይፋ ተደርገዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በመርሃ-ግብሩ እንደገለጹት፤ መተግበሪያዎቹ ኢትዮጵያ በዘመናዊነት ጉዞዋ ለምታስመዘግበው ውጤት ማሳያ ናቸው።


 

በተለይም የፖስታ ገበያ መተግበሪያ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚያጋጥሟቸውን የመገበያያ መሰናክሎች በማቃለል በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳግማዊ ኃይልዬ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ መልዕክቶችንና ዕቃዎችን ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ በማድረስ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ መሆኑን ገልፀዋል።

ዛሬ ይፋ የሆኑት መተግበሪያዎች ደግሞ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት ወደ ፊት የሚያራምዱ መሆናቸውን ነው ያብራሩት።

የሳጥን አልባ የፖስታ ደንበኞች የግል የፖስታ ሳጥን ቁጥር ሳይኖራቸው የራሳቸውን ስልክ ቁጥር እንደ ፖስታ አድራሻ እንዲጠቀሙ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።


 

ደንበኞች የተላከላቸው ዕቃ ወይም መልዕክት መድረሱን በስልካቸው አማካኝነት ፈጣን መረጃ ያገኛሉ።

ዕቃዎችን ደንበኞች ባሉበት አድራሻ እንዲደርሷቸው በማድረግም ቀደም ሲል የነበረውን የገንዘብ ብክነትና እንግልትም የሚያስቀር መሆኑን አስታውሰዋል።

አዲሱ አሰራር ድርጅቱ ካለው ረጅም ልምድ ጋር ተዳምሮ የደንበኞችን እርካታ ከፍ እንደሚያደርገው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም