ቀጥታ፡

በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተከናወነው ስራ ውጤታማ ነው 

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና በግብርና ምርቶች የውጪ ምንዛሪን ለማስገኘት የተከናወነው ስራ ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ።   

የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች በሲዳማ ክልል በሀዋሳ ዙሪያና ሸበዲኖ ወረዳዎች የሚገኙ የበጋ መስኖና የቡና ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።


 

በጉብኝቱ ወቅት ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ፤  በሁለቱ ወረዳዎች አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማሳደግ እየሰሩ ያሉት ስራ በትክክለኛው መንገድ እየተጓዙ ስለመሆኑ ማየት ችለናል ብለዋል።

ሁለቱ ወረዳዎች ቀደም ሲል  ሴፍቲኔት ታቅፈው የሚደገፉ ቤተሰቦች ያሏቸው ቀበሌዎች ይበዙባቸው እንደነበር መረዳታቸውን ገልጸዋል።


 

ክልሉ  ከፌዴራል መንግስት ጋር በመቀናጀት በመስኖ ልማት እንዲሳተፉ የመስኖ ውሀ ተቋማትን በመገንባትና የግብዓት አቅርቦት በማሟላት በግብርና ኤክስቴንሽን ስራው ድጋፍ በመደረጉ ውጤታማ መሆን እንደቻሉ መመልከታቸውን  ተናግረዋል።


 

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና በግብርና ምርቶች የውጪ ምንዛሪን ለማስገኘት  በክልሉ  የተከናወነው ስራ ውጤታማ ሆኖ እንዳገኙት አመላክተዋል።    

እንደ ሀገር በተያዘው ዓመት  ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመጀመሪያ ዙር የበጋ መስኖ በሆርቲካልቸር በማልማት 250 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ እንደተገባ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

በክልሉ አርሶ አደሮች ቀደም ሲል በቆሎና ሌሎች ሰብሎችን በማልማት ከሚያገኙት ጥቅም የበለጠ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲምና ሌሎች አትክልቶችን በማልማት ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉም ማየታቸውን ገልጸዋል።


 

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው፤  በክልሉ ያለውን አቅም በመለየት በእርሻው ዘርፍ 19 ፓኬጆችን በማዘጋጀት ወደ ስራ እንደተገባ ተናግረዋል።


 

ከእነዚህ ፓኬጆች ስድስቱ ቡና፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በተያዘው ዓመት በበጋ መስኖ 80 ሺህ ሄክታር መሬት በመጀመሪያ ዙር ለማልማት ታቅዶ እስከ አሁን 54 ሺህ ሄክታር መልማቱን ገልጸዋል።

በጉብኝቱ የፌዴራል፣ የክልሉ፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም