የዘላቂ ልማት ጥበቃ ፕሮጀክት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የዘላቂ ልማት ጥበቃ ፕሮጀክት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አስችሏል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ሲተገበር የቆየው ግብርና ላይ የተመሰረተ የዘላቂ ልማት ጥበቃ ፕሮጀክት የአፈር ለምነትን በመጨመር ረገድ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
በኢትዮጵያ እኤአ 2022-2025 ሲተገበር የቆየው ግብርና ላይ የተመሰረተ የዘላቂ ልማት ጥበቃ ፕሮጀክት(SCASI) አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።
ፕሮጀክቱ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች ላይ ሲተገበር መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብትና የአፈር ለምነት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሊሬ አብዩ እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን፣ የሰብል ማፈራረቅ ዘዴንና የአርሶ አደሩን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ይህም በተተገበረባቸው አካባቢዎች የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና ድህነትን በመቀነስ ረገድ ውጤታማ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዓለም የበቆሎና የስንዴ ምርምር ማዕከል የኢትዮጵያ አስተባባሪ ብርሃን አብዱልቃድር በበኩላቸው፤ ማዕከሉ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የሰብል ዝርያዎችን በማውጣትና በማስፋፋት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በሜካናይዜሽንና በምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ የተሰሩ ሥራዎች የአርሶ አደሩ ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በተለይ የስንዴ እና የበቆሎ ዝርያን በማሻሻል ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ እንደ የአካባቢ ስነ-ምህዳር የሚውሉ ዝርያዎችን እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ቀኛዝማች መስፍን ፤ፕሮጀክቱ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ያመጣው ለውጥ በተግባር መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰብል ልማት ጥበቃና ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ዳይሬክተር ፍቅሩ አቡን በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በክልሉ ሁለት ወረዳዎች መተግበሩን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ የተገኘውን መልካም ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።