ቀጥታ፡

የመደመር መንግስት ሁሉም ዜጋ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሥርዓት እየገነባ  ይገኛል

ባሕርዳር፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦የመደመር መንግስት ሁሉም ዜጋ  እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆንበትን ስርዓት እየገነባ ይገኛል ሲሉ  የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

በባሕርዳር  ከተማ 123 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ  የተገነባ የሴቶችና ህፃናት ማገገሚያ ማዕከል ዛሬ ተመርቋል።

ማዕከሉን የክልሉ የጤና ፣ የሴቶች፤ ወጣቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች በጋር በመተባበር እንዳስገነቡት ተገልጿል።


 

በምረቃው ሥነ- ሥርዓት ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የመደመር መንግስት ሁሉም ዜጋ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆንበት ሥርዓት እየገነባ ይገኛል።

‎በባሕርዳር ከተማ የተገነባው የማገገሚያ ማዕከልም የመደመር መንግስት በተለይ  ለተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሰጠው ትኩረት አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

‎በተቋማት ትብብር በአጭር ጊዜ የተገነባው ማገገሚያ ማዕከሉ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናትን ፈጥኖ በማስገባት ወደ ቀደመ ሕይወታቸው እንዲመለሱ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

‎ሚኒስቴሩ ማዕከሉ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ በቀሳቁስና ሌሎች የድጋፍ ዓይነቶች አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። 

‎‎በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤  ማዕከሉ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናት እንዳያገግሙ  በመደገፍ ምቹ ሁኔታ  እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

‎በቀጣይም ተመሳሳይ ማዕከላትን ወደ ሌሎች ከተሞች የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

‎የክልሉ ሴቶች፣  ወጣቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ ፤ የማዕከሉ መገንባት ትልቅ  ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።


 

‎ማዕከሉ ‎በሶስት ሺህ 200 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በሶስት ወራት ውስጥ የተገነባ መሆኑን  የገለጹት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ ናቸው።

በውስጡ የመኝታ፣ የሕክምና፣ የስልጠና፣ የአስተዳደርና ሌሎች አገልግሎቶች የሚሰጡ 35 ክፍሎችን  ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

በ‎‎ተመሳሳይም በጎንደር ከተማ መሰል ማእከል እየተገነባ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን  በደሴና በሌሎች ከተሞች በቀጣይ ተደራሽ ለማድረግ ቢሮው ከክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮና የከተማ አስተዳደሮች ጋር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

‎የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)‎ እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በባሕርዳር ፈለገ ሕይወት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግቢ የተቋቋመውን ሁለንተናዊ የለውጥ መሪነት ስርዓተ ፆታ እኩልነት የስልጠና ማዕከልንም ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም