ቀጥታ፡

ለሕብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት በተጓዳኝ ሰላምን ለማፅናት ድጋፋችንን እናጠናክራለን- አሽከርካሪዎች 

ደብረብርሃን፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ለሕብረተሰቡ  ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ጎን ለጎን ሰላምን ለማፅናት  ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የደብረ ብርሃን ከተማ  የታክሲ አሽከርካሪዎች ገለጹ።   

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ከታክሲ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ጋር በሰላም ማስከበር ላይ ዛሬ ተወያይቷልⵆ 

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ዓለሙ አሽኔ፤ በትራንስፖርት ዘርፉ ቀልጣፋ አገልግሎት ለሕብረተሰቡ  ከመስጠት በተጓዳኝ  ዘላቂ ሰላምን  ለማስፈን የበኩላቸውን  ሲወጡ እንደቆዩ ተናግረዋል።


 

ይህንን በማጠናከር  ከፖሊስ  ጋራ  በመተባበር  ወንጀልን ለመከላከል በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ሸዋለም ግዛቸው በበኩላቸው፤  የከተማዋ እድገት እንዲፋጠን  የትራንስፖርቱ ዘርፍ ያለውን ድርሻ ለማሳካት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

መንግስት የሚያወጣውን ደንብና መመሪያ አክብረው በመስራት  በአካባቢው የሰፈነውን  ሰላም በዘላቂነት ለማፅናት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት በመሳተፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተሳታፊዎቹ  ገልጸዋል።


 

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሀላፊ አቶ ዳንኤል እሸቴ በበኩላቸው፤ ከከተማው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር በተከናወነው ሕግ የማስከበር ስራ ሰላምን  ማስጠበቅ  መቻሉን ተናግረዋል። 

ሰላምን አስጠብቆ በማዝለቅ የከተማዋን ልማት ለማፋጠን እየተከናወነ ባለው ስራ ውስጥ የታክሲ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የዛሬው መድረክ ዓላማም የታክሲ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች ሕገወጥነትን በመከላከል ፈጣንና ውጤታማ አገልግሎት ለሕብረተሰቡ እንዲሰጡ ለማስገንዘብ ጭምር እንደሆነ  ተናግረዋል።


 

የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ደጀኔ ልመንህ፤  የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማፅናት  የነዋሪዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋልⵆ

ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች በሰላም ማስጠብቅና በወንጀል መከላከል  የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ለሕብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በውይይቱ ላይ የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖችን ጨምሮ ሌሎችም አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም