ቀጥታ፡

በከተማዋ መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ በቂ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች እየቀረቡ ነው

አዳማ ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦በአዳማ ከተማ መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ በቂ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች እየቀረቡ መሆናቸውን የከተማዋ አስተዳደር ገለጸ። 

የዘንድሮውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ሸማቾችንና አምራቾችን ለማገናኘት ያለመ የንግድ ትርዒትና ባዛር በአዳማ ተከፍቷል።


 

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ማቲያስ ሰቦቃ በወቅቱ እንደገለፁት፤ በከተማዋ መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ በቂ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች እየቀረቡ ነው። 


 

ለዚህም የአዳማ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የግብርናና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች የዋጋ ንረትና ገበያ ማረጋጋት ላይ አበረታች ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዚህም በተለይ ወተት፣ እንቁላል፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የምግብ ዘይትና ሌሎች የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የንግድ ትርዒትና ባዛሩ ሸማቹን  ከአምራቹ ጋር በቀጥታ በማገናኘት በበዓል ምክንያት የግብርና ምርቶችና ሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ እንዳይኖርና ገበያን ለማረጋጋት በማለም የተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል። 

በመክፈቻው ላይ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ የአዳማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሸናፊ አጀማ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የኑሮ ውድነትን ለመግታት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። 


 

በዚህም አምራቹ በቀጥታ ምርቱን ለሸማቹ እንዲያቀርብ በማድረግ የዋጋ ንረትን በመቀነስ ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ግብይት እንዲፈፅም እየተደረገ መሆኑን አክለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የግብርና ምርቶች የመሸጫ ማዕከላት በመገንባት የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ገልጸው በዚህም ስንዴ፣ ጤፍ፣ ዱቄት፣ የወተት ተዋፅኦን ጨምሮ ዶሮና እንቁላል እንዲሁም ሌሎች ምርቶች ቀርበዋል ብለዋል።   

የአዳማ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስራ አስፈፃሚ አቶ ብዙነህ ግርማ በበኩላቸው፤ኢንቨስትመንት ግሩፑ ገበያን በማረጋጋት ረገድ በቀን ሁለት ሺህ 500 ሊትር ወተትና እንቁላል ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል። 


 

በተጨማሪም ግሩፑ የገበያ ትስስር በመፍጠር የግብርና ምርቶችና ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ እያደረገ መሆኑን ጠቅሶ ከከተማዋ የንግድ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር ባዛር ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም