ቀጥታ፡

እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል-ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 21/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመ ጀምሮ ባከናወናቸው ተግባራት በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ሀገራዊ ምክክሩን ለመምራት ገለልተኛ ሆኖ መዋቀሩን ያስገነዘቡት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ፤ እስካሁን ስኬታማ ተግባራት ማከናወኑን ለኢዜአ ጠቁመዋል።

በዚህም መሠረት ባለድርሻ አካላት ተለይተው በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድ በርካታ ውጤቶች የተገኙባቸው ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።

አጀንዳ የተሰበሰበበት መንገድ በርካቶች የተስተናገዱባቸው መድረኮች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህም የዴሞክራሲ ልምምድን በማሳደግ የምክክር ሂደት እንዲዳብር የጎላ ሚና አለው ብለዋል።

የምክክር ሂደቱ የኢትዮጵያውያን እንዲሆንና ባለድርሻ አካላት የሂደቱ ባለቤት እንዲሆኑ የተሠሩ ሥራዎችም ውጤት የተገኘባቸው መሆናቸውን ነው ያስገነዘቡት።

በግልጽና ገለልተኛ አሠራር አካታችና አሳታፊ በሆነ መንገድ ተሳታፊዎችን መለየት መቻሉ ከተገኙ ውጤቶች መካከል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በውክልና የመሳተፍ ልምምዶችን፣ዴሞክራሲያዊ ባሕርይን የማምጣቱ ጉዳይም ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው መሆኑን አመላክተው፤ 93 በመቶ የኢትዮጵያ ወረዳዎችን በምክክር ሂደቱ ማሳተፍ መቻሉን አመላክተዋል።

በሕዝቡ፣በባለድርሻ አካላት፣ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም ጭምር ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ተቀባይነት እንዲኖረው የተደረገው ጥረት ውጤት የተገኘበት መሆኑንም ነው ያረጋገጡት።

በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው በሂደት ከኃይል አማራጭ ይልቅ ምክክር የተሻለ ውጤታማ ያደርጋል የሚለው አስተሳሰብ በበርካቶች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ገልጸው፤ ይህም ባለፉት ጊዜያት የተደረጉ ጥረቶች ውጤት ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ በቅርቡም በትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት እንደሚያካሂድ ገልጸው፥ በተቀሩት ሁሉም ክልሎች፣በአዲስ አበባ ከተማ፣ በድሬዳዋ አሥተዳደር፣ በዳያስፖራው ማኅበረሰብ እና በፌደራል ደረጃ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ተግባራት በስኬት መከናወናቸውንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም