የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታና ለብሔራዊ መግባባት መሠረት የሚጥልበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታና ለብሔራዊ መግባባት መሠረት የሚጥልበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦የሀገራዊ ምክክር ሂደት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታና ለብሔራዊ መግባባት መሠረት የሚጥልበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ጠንካራ የሀገረ መንግስት ግንባታን የሚያፋጥኑ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ለዚህም አካታች ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማከናወን፣ የህግ የበላይነት የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት እንዲሁም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የረጅም ዓመት ታሪክ ውስጥ ብሔራዊ መግባባት አለመስፈን፣ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ አለመፍታት እና ኋላ ቀር የፖለቲካ አመለካከት በሀገረ መንግስቱ ውስጥ የታዩ ስብራቶች መሆናቸውን አውስተዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ሂደትን ማሳካት፣ ምርጫን በተሳካ መንገድ ማካሄድ፣ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ የህግ የበላይነትን ማስፈን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትሆን ሀገር ለመገንባት ያስችላል ብለዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ሂደት ውጤታማ መሆን የኢትዮጵያን የቆዩ ችግሮች ትርጉም ባለው መልኩ እንደሚፈታ የገለጹት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያን ስብራቶች ከመጠገን አኳያም ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
ምክክሩ ለብሔራዊ መግባባት ወሣኝ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ለመፍጠር ስለሚያግዝ ሁሉም በንቃት መሳተፍ እንዳለበት ጠቅሰው፤ ለግጭት መነሻ የሚሆኑ ጉዳዮችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትም ትክክለኛ አማራጭ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክር ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ ለዘላቂ ሰላምና ለብሔራዊ መግባባት መሰረት በሚጥልበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል ብለዋል።
የተሳካ ሀገራዊ ምክክር ማከናወን ሁሉም ዜጎች የተግባቡበት የጋራ ሕገ-መንግስት እውን ለማድረግና ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ስለሚረዳ የሁሉንም የነቃ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ነው የተናገሩት።
በኢትዮጵያ ኋላቀር የፖለቲካ ባህልን ለመቀየር፣ አዎንታዊ የሰላም ባህልን ለመገንባት እንዲሁም ኢትዮጵያውያን በተፈጥሮ ሃብቶቻቸው ሰርተው እንዲለወጡና የበለጸገች ሀገር እንዲገነቡ መሰረት ይጥላል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በትግራይ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብና የተሳታፊዎች ልየታ ለማከናወን የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፤ ለዚህም ከክልሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች መደረጋቸውን ለምክር ቤቱ ከቀረቡ ሪፖርቶች መገንዘብ እንደሚቻል ተናግረዋል።