ቀጥታ፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥርዓተ ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ ረቂቅ አዋጅን አጸደቀ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥርዓተ ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባ አካሂዷል።

የአዋጁን አስፈላጊነትም የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት እንዲሁም የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በጋራ ያዘጋጁት ሪፖርት ለምክር ቤቱ ቀርቧል።


 

በምክር ቤቱ የሁለቱን ቋሚ ኮሚቲ የውሳኔ ሃሳብ ሪፖርትም የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲያ አህመድ አቅርበዋል፡፡

በሪፖርቱም ረቂቅ አዋጁ የሥርዓተ ምኅዳር ደኅንነትና ዘላቂነትን በማረጋገጥ ጥቅምና የተፈጥሮ አያያዝን ለማሻሻል ወሳኝ መሆኑን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሥርዓተ ምህዳር አገልግሎት ዋጋ ላይ የተፈጠረው ሳይንሳዊ ግንዛቤ ማደግ ለአዋጁ መውጣት መነሻ ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል።

የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎቶች ለኢኮኖሚ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በፖሊሲዎችና በውሳኔ አሰጣጥ ላይ እየተንጸባረቀ የሚገኝ መሆኑም ተገልጿል።


 

በዚህም የሥርዓተ ምኅዳርን በዘላቂነት ለማስተዳደር የሚያስችል የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ የሕግ ማዕቀፍና የአሰራር ስርዓቶችን መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ በረቂቅ አዋጁ የውሳኔ ሀሳብ ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ ቢሻሻሉና ቢካተቱ ያሏቸውን ምክረ ሃሳቦች በጥያቄና አስተያየት አቅርበዋል።

በቀጣይም የሥርዓተ ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ ረቂቅ አዋጅ የትግበራ አፈፃጸም ውጤታማነትን ለማስጠበቅ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባው የሥርዓተ ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ ረቂቅ አዋጅን በመመርመር በአዋጅ ቁጥር 1401/2018 ዓ.ም በአንድ ድምፅ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም