በክልሉ የቡና ምርትን ከቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር በስፋት ለማስተዋወቅ በጋራ መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የቡና ምርትን ከቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር በስፋት ለማስተዋወቅ በጋራ መስራት ይገባል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናን በስፋትና በጥራት በማምረት በዓለም ደረጃ ለማስተዋወቅ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
ቱሪዝም ሚኒስቴር ከታህሳስ 20 ቀን 2018 ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት "የቡና ቱሪዝምን" በተመለከተ ያዘጋጀውን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የጉብኝት መርሃ ግብር በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ባለሙያዎቹ በሁለተኛው ቀን ውሎአቸው በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን ይርጋ ጨፌ ገደብ ወረዳ የቡና አመራረት ሂደትን የተመለከተ ጉብኝት አካሂደዋል።
በዚሁ ወቅት የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ወይኒቱ መላኩ፤ ክልሉ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የፖሊሲና ስትራተጂ ማሻሻያዎች ከማድረግ ጀምሮ በርካታ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በተለይም የክልሉን የቡና ቱሪዝም ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ከክልሉ በርካታ ፀጋዎች መካከል አንዱ የሆነው የቡና ልማት ማህበራዊ እሴትን ከማጠናከር ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።
በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ ያለውን የቡና እምቅ አቅም ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ የክልሉ ተወላጆችና የዘርፉ ምሁራን በተለያዩ የዓለም ሀገራት በመዘዋወር የንግድ ትስስር የመፍጠር ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ አንስተዋል።
የቡና ምርታማነትን አሁን ካለው በተሻለ ለማሳደግ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህ ደግሞ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
በክልሉ ያለውን የቡና ልማት ከቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር በስፋት ለማስተዋወቅ በጋራ መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።