በየአካባቢው ያሉ ሀብቶችን በማልማት የተገኙ ውጤቶች ሁለንተናዊ ዕድገትን ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚያሳዩ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በየአካባቢው ያሉ ሀብቶችን በማልማት የተገኙ ውጤቶች ሁለንተናዊ ዕድገትን ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚያሳዩ ናቸው
ሚዛን አማን፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ በየአካባቢው ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለይቶ በማልማት የተገኙ ውጤቶች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚያሳዩ መሆናቸውን የክልል አፈ ጉባኤዎች ገለጹ።
የክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች አፈ ጉባኤዎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
አፈ ጉባኤዎቹ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ያለውንና የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የደንቢ ሐይቅ ሎጅ፣ የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ የግንባታ ሂደት እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ አፈ ጉባኤዎች፤ በየአካባቢው ተደብቀው የቆዩ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለይቶ በማልማት የተገኙ ውጤቶች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ማረጋገጥ እንደሚቻል ተስፋ የሰነቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎ እንዳሉት፤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ሁለንተናዊ ዕድገትን የሚያረጋግጡ ናቸው።
ከዚህ ቀደም የነበሩ ነገር ግን ያልተጠቀምንባቸውን የተፈጥሮ ጸጋዎችን በማልማት ወደሚታይ ፍሬ መቀየር መቻሉ ነገን በተሻለ ለውጥ አሻግረን እንድናይ አስችሎናል ብለዋል።
እንደ ደንቢ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ያሉ ሀብቶችን ከየክልሉ ለይቶ ማየት የሚችል መንግስት በመኖሩ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፣ ልማቱን ለማስፋፋት የየአካባቢው አመራር ከህዝብ ጋር ተባብሮ መሥራት አለበት ብለዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ተዘዋውረው ያዩት የተፈጥሮ ሀብት ወደ ኢኮኖሚ ሲቀየር በኢትዮጵያ ዕድገት ላይ ጉልህ ሚና ያበረክታል ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አብዲ ሙክታር ናቸው።
በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ኢኒሺዬቲቭ ያለ የተፈጥሮ ሀብት በማልማት የቱሪዝም ኢኮኖሚን ለማጠናከር እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተሠሩና በመሠራት ላይ ያሉ ተፈጥሮን የማልማት ፕሮጀክቶች በቱሪዝም ዘርፍ የገቢ ምንጭና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እየሆኑ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ሀብት አውቆ ካለማ በእድገት ወደፊት ከመጡ የዓለም ሀገራት ተርታ የመሰለፍ እድል ይኖረናል የሚል እምነታቸውንም ገልጸዋል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አስካለ አልቦሮ በበኩላቸው፤ በሌሎች አካባቢዎች የሌሉ የልማት ተሞክሮዎችን በክልሉ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
በተለይ ተፈጥሮን የመጠበቅና የማልማት ልምድን ወደሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ማስፋፋት እንደሚገባ ገልጸው፣ ሕዝብን በማስተባበር የተሻለ ልማት ለማምጣት የተጀመሩ ጥረቶች መጠናከር አለባቸው፤ እኛም የሚጠበቅብንን እንወጣለን ብለዋል።