ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በከተሞች መካከል ጤናማ የውድድር መንፈስ እንዲፈጠር አስችሏል 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች መካከል ጤናማ የውድድር መንፈስ እንዲፈጠር ማስቻሉን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

“የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት” በሚል መሪ ቃል 10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በቅርቡ በአፋር ክልል ሰመራ-ሎጊያ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል። 

ፎረሙ ከተሞች ልምድ እንዲለዋወጡ፣ ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ እና ለሀገር ዕድገት ያላቸውን ሚና እንዲፈትሹ የሚያስችል ሰፊ መድረክ መሆኑም ተመልክቷል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ፎረሙ ከተሞች እንዲነቃቁ በማድረግ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። 

በተጨማሪም በከተሞች መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር ለሕዝቦች አብሮነትና ለሀገራዊ ትርክት ግንባታ ገንቢ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከተሞች በራሳቸው ጸጋ የማደግ ትልቅ አቅም እንዳላቸው ገልጸው፤ የመደመር መንግሥት ከተሞችን የድህነትና የመልካም አስተዳደር እጦት ማሳያ ከመሆን አውጥቶ የብልጽግና ማዕከልና ተምሳሌት ለማድረግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል። 

በዚህ እሳቤ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችም የኢትዮጵያን አዲስ ከፍታ የሚያሳዩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት ከተሞችን የመለወጥ ራዕይ በተግባር እየተገለጠ  እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

ስትራቴጂ በመንደፍና በፖሊሲ በመደገፍ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ከተሞች የብልጽግና ተምሳሌት እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም