የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ተዓማኒ፣ ጥራት ያለውና ጊዜውን የጠበቀ የጤና መረጃ ለማግኘት ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ተዓማኒ፣ ጥራት ያለውና ጊዜውን የጠበቀ የጤና መረጃ ለማግኘት ያስችላል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ተዓማኒ፣ ጥራት ያለውና ጊዜውን የጠበቀ የጤና መረጃ ማግኘት የሚያስችል መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለጹ፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅን አተገባበር በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 1370/2017 መሰረት ከፌደራል እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ራሱን የቻለ አደረጃጀት እንዳለው ይታወቃል፡፡
በዚህም አገልግሎቱ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ የማከናወን፣ የመምራት፣ የማስተባበር፣ የመደገፍ፣ የምዝገባ መረጃዎችን የማስተዳደር እና የማደራጀት፣ በብሔራዊ ደረጃ በመረጃ ቋት አደራጅቶ የመያዝ ሀላፊነት ተሰጥቶታል።
አዋጁ ዜጎች በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የሚያገኙትን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑ ታምኖበት ተዘጋጅቷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ የጤና ተቋማትን ብሔራዊ ማንነት ማዕከል የሚያደርግ ነው፡፡
በጤና ተቋማት የልደትና ሞት ምዝገባ እንደሚከናወን ገልጸው፤ ምዝገባው በዲጂታል የተደገፈ መሆኑ የተጣራ የጤና መረጃ ማግኘት ያስችላል ብለዋል፡፡
በሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ የሚገኘው የጤና መረጃ ለተወለዱ ህፃናት የሚያስፈልገው የክትባት፣ የሥነ ምግብ አልያም የክትትል ሥርዓቱ ምን መምሰል እንዳለበት ማወቅ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ለእናቶች የሚያስፈልገውን አገልግሎት መለየት ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
በሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ የሞት መንስኤዎችን መለየት የሚያስችል መረጃ እንደሚሰጥ የገለጹት ዶክተር ደረጀ፤ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን አፈፃፀም መገምገም ያስችላል ብለዋል፡፡
የተደራጀ የዲጂታል ምዝገባ በማካሄድ ተዓማኒ፣ ጥራት ያለውና ጊዜውን የጠበቀ የጤና መረጃ ማግኘት እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡
የጤና ፕሮግራሞችን ተፈፃሚነት ለመከታተል፣ እቅዶችን ለማውጣት እና ሥራዎችን ለመገምገም አስፈላጊ የመረጃ ምንጭ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡